የኢትዮጵያ አየር መንገድ በፈረንጆች 2017/18 ዓመት ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፉን አስታወቀ

3037

አዲስ አበባ ነሃሴ 4/2010 የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዘንድሮው አመት 6 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ።

ትርፉ መንገደኞችን በማጓጓዝ፤በእቃ ጭነትና በሌሎች የሎጅስቲክስ አገልግሎቶችን በመስጠት መሆኑን አየር መንገዱ ገልጿል።

አየር መንገዱ የ2017/18 አጠቃላይ አፈጻጸሙን አስመልክቶ ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል።

ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ተወልደ ገብረ ማሪያም በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ መሻሻል እያሳየ ይገኛል።

በዚህም በዓለም አቀፍና በአፍሪካ ከሚገኙት አየር መንገዶች በምሳሌነት የሚነሳ መሆኑን ነው የገለጹት።

በዚህም በ2017/18 የፈረንጆች ዓመት 6 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን የገለጹት አቶ ተወልደ ከአምናው ጋር ሲነጻጻር 25 በመቶ እድገት መመዝገቡንም ተናግረዋል።

አየር መንገዱ በዓመቱ 10 ነጥብ 6 ሚሊዮን መንገደኞችን ያጓጓዘ ሲሆን በመንገደኞች ብዛት ከዓምናው ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ21 በመቶ እድገት አሳይቷል።

በእቃ ጭነትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ደግሞ 400 ሺህ 339 እቃዎችን በማጓጓዝ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ18 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን አቶ ተወልደ ተናግረዋል።

በበጀት አመቱ አየር መንገዱ አስራ አራት አዳዲስ አውሮፕላኖችን ግዥ በመፈጸም  አጠቃላይ ያለውን የአውሮፕላን ቁጥር 100 ማድረሱም ተገልጿል።

በዚሁ ዓመት በስዊዘርላንድ፤በአሜሪካ፤በናይጀሪያ፤አርጀንቲና፤በዴሞክራቲክ ኮንጎና በማዳጋስካር ተጨማሪ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችንም መክፈት መቻሉን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የአየር መንገዱን አቅም ለማሳደግ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የባለቤትነት ድርሻ በመግዛት ገቢውን እያሳደገ እንደሚገኝም ዋና ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ የነበረው የአውሮፕላን ዋጋ ጭማሪና በአንዳንድ የአፍሪካ አገራት የነበረው አለመረጋጋት ለስራቸው እንቅፋት እንደነበርም አንስተዋል።

ሆኖም ግን አየር መንገዱ ችግሮችን ተቋቁሞ በመስራት የአራተኛ የኮከብ ማዕረግ ማግኘቱን ተናግረዋል።

በቀጣይም በተለያዩ አገራት መዳረሻውን በማስፋት እንዲሁም የባለቤትነት ድርሻዎችን በመግዛት አሰራሩን የበለጠ በማዘመን ኢኮኖሚውን ለማሳደግ እንደሚሰራ አቶ ተወልደ  ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአወሮፓዊያን አቆጣጠር በመጪው ጥቅምት ሥራ ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀውን አዲሱ የቻድ አየር መንገድን የ49 በመቶ ድርሻ ሊይዝ እንደሆነ መዘገባችን ይታወሳል።

አዲስ የተቋቋመው የቻድ አየር መንገድ 51 በመቶ የባለቤትነት ድርሻን የቻድ መንግስት የሚይዘ ሲሆን ከአትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በሽርክና ለመስራት ውይይት እየተካሄደ መሆኑም ተመልክቷል።

መቀመጫው በኬንያ የሆነው ‘ዘ ኢስት አፍሪካ ‘ እንደዘገበው በሁለቱ አየር መንገዶች መካከል ተግባራዊ በሚሆነው የጋራ ትብብር መሰረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመካከለኛው አፍሪካ ለሚሰጠው የበረራ አገልግሎት የቻድ አየር መንገድን ማዕከል አድርጎ ይሰራል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቻድ በተጨማሪ የጅቡቲን፣ የኢኳቶሪያል ጊኒን እና የጊኒን አየር መንገዶች በሽርክና ለመያዝ ከአየር መንገዶቹ ጋር እየተነጋገረ መሆኑም ተገልጿል።

ከዚህ በፊት አየር መንገዱ የቶጎ አየር መንገድን 40 በመቶ፤ የማላዊ አየር መንገድን ደግሞ 49 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ይዞ በሽርክና እየሰራ ይገኛል።

ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ተዘግቶ የቆየውንና በዚህ ዓመት ሥራ ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀውን የዛምቢያን አየር መንገድ 45 በመቶ ድርሻ ባለፈው ጥቅምት ወር መግዛቱም ተመልክቷል።

በገቢና በትርፋማነቱ ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቀጣይም የሞዛንቢክ አየር መንገድን ሙሉ ባለቤትነት በመያዝ  ለማስተዳደር እቅድ እንዳለውም ተገልጿል።