በአማራ ክልል የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብርን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

105
ባህር ዳር ነሀሴ 4/2010 የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር የመሰረታዊ ጤና አገልግሎት ማስፈጸሚያ ስልት ሆኖ እንዲቀጠል በአዳዲስ አሰራሮች ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ። ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ክልል አቀፍ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ማሻሻያ የንቅናቄ መድረክ ትናንት በባህርዳር ተካሂዷል። የጤና ቢሮው ኃላፊ ዶክተር አበባው ገበየሁ በዚህ ወቅት እንደገለጹት ባለፉት 12 ዓመታት መከላከልን መሰረት አድርጎ የተካሄደው የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል። የእናቶችና ህፃናት ሞት፣ እንዲሁም  ተላላፊ በሽታዎች እየቀነሱ እንዲመጡና የህብረተሰቡ የጤና ችግር ወደማይሆኑበት ደረጃ እንዲደርሱ አስችሏል። ነፍሰጡር እናቶች ቤት ውስጥ እንዳይወልዱ ከሴቶች አደረጃጀቶች ጋር የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ባከናወኑት ስራም 270 ሺህ የሚሆኑ እናቶች ዘንድሮ በጤና ተቋማት እንዲወልዱ ተደርጓል። ህብረተሰቡ የግልና የአካባቢውን ንፅህና እንዲጠብቅ በተደረገው ጥረትም  የክልሉ የመፀዳጃ ቤት ሽፋን 80 በመቶ ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል። ሆኖም አሁን በሀገር ደረጃ እየታየ ካለው ለውጥና ከህዝቡ የአኗኗር ደረጃ ጋር የተጣጣመ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም  ማስፈጸሚያ ስልት በመንደፍ መስራት ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው። "በዚህም የባለሙያዎችን አቅምና ክህሎት በማሳደግ የሳንባ ምች፣ ወባ፣ ተቅማጥና ለሌሎች በሽታዎች ህክምና እንዲሰጡ በማስቻል እንደ ደም ግፊት፣ ስኳርና ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለማከም በሚያስችል መልኩ ማዘጋጀት ይገባል" ብለዋል። ዶክተር አበባው እንዳሉት የንቅናቄ መድረኩ ዓላማም  የተመዘገበው ውጤት ለማጠናከርና አዳዲስ መርሃ ግብሮችን አካቶ በቀጣይ እንዲሰራ  ያለመ ነው። በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የጤና ኤክስቴንሽንና የመጀመሪያ ደረጃ ህክምናና እንክብካቤ ምክትል ዳይሬክተር አቶ እስራኤል አታሮ በበኩላቸው ተላላፊ በሽታዎችን በሀገር ደረጃ በመቀነስ በኩል የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሙ ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል። የሁለተኛው ትውልድ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በሀገር ደረጃ  እንደሚተገበርና ይህም የባለሙያዎችን የዕውቀትና ክህሎት በማሻሻል አዳዲስ መርሃ ግብሮች ለማሳካትና ህዝቡ የሚፈልገውን አገልግሎት በቅርበት ለመስጠት የሚያስችል ነው። ቀደም ሲል በጤና ክስቴንሽን ፕሮግራም በተከናወነው  ስራ ኢትዮጵያ የህፃናት ሞትን በመቀነስ የምዕተ ዓመቱ ግብ ማሳካት  እንዳስቻላትም ተመልክቷል። በአካባቢያቸው በተከናወነው የጤና ኤክስቴንሽን ስራ በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶችን ሽፋን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 99 በመቶ ማድረስ መቻሉን የገለጹት ደግሞ በደቡብ ወሎ ዞን የጃማ ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሃመድ የሱፍ ናቸው። "የማሻሻያ ንቅናቄ መድረኩ መጀመሩም  ተቀዛቅዞ የቆየውን የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በማነቃነቅ ይበልጥ ውጤታማ ስራ እንዲከናወን ያስችላል" ብለዋል። ከሰሜን ጎንደር ዞን አዲአርቃይ ወረዳ የከበር ማርያም ቀበሌ ጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ ወይዘሮ ሙሉወርቅ ካሳ በበኩላቸው የልማት ቡድኖች የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጆችን በመተግባር ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል። በሴቶች የልማት ቡድኖች አማካኝነት የተጠናከረ ስራ በመከናወኑም ዘንድሮ በቀበሌው የሚገኙ 193 ነፍሰ ጡር እናቶች በጤና ተቋማት እንዲወልዱ ማስቻሉን አስረድተዋል። ለአንድ ቀን በተዘጋጀው የንቅናቄው መድረክ  ከፌዴራል፣ ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ የጤናው ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።                      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም