በጋምቤላ ክልል የተጀመረው የመንደር ማሰባሰብ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - የክልሉ ርእሰ መስተዳድር

68
ጋምቤላ  ነሃሴ 4/2010 በጋምቤላ ክልል የመንደር ማሰባሰብ መርሃ ግብሩን በማጠናከር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የበለጠ ለማረጋገጥ እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መሰተዳድር አቶ ጋትሉዋክ ቱት አስታወቁ። በመንደር የተሰባሰቡ እማወራዎችና አባወራዎች በበኩላቸው በመንደር መሰባሰባቸው የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈ ወደ ተሻለ የግብርና ልማት ስራ በመግባት ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ገልፀዋል። ርዕሰ መሰተዳደሩ አቶ ጋትሉዋክ ቱት ሰሞኑን የተለያዩ የመንደር ማዕከላትን በጎበኙበት ወቅት እንደገለጹት በክልሉ የተጀመረውን የመንደር ማሰባሰብ መርሃ ግብር በማጠናከር የህዝቡን ዘላቂ ተጠቀሚነት የማረጋገጡ ስራ ተጠናከሮ ይቀጥላል። በክልሉ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ የተካሄደው የመንደር ማሰባሰብ መርሃ ግብር ህዝብን የትምህርት፣ የጤና፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የመንገድና ሌሎች የመሰረተ ልማት አገልግሎት ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ተጨባጭ ውጤት የተገኘበት መሆኑን ተናግረዋል። ''ከዚህም ባለፈ ህዝቡ የተፈጠረለትን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ወደ ተሻለ የግብርና ልማት ሰራዎች በመግባት የምግብ ዋትናቸውን ማረጋገጥ ጀምሯል'' ብለዋል ። በአሁኑ ወቅት በተወሰኑ የክልሉ አካባቢዎች ግብርና ቴክኖሎጂ፣ የመሰረተ ልማት አጠቃቀምና አያየዝ፣ የጤና ኤክስቴንሽን ተግባራዊ በማድረግ ወደ ተሻለ የአኗኗር ዘይቤ የተሸጋገሩ ሞደል የመንድር ማዕከላት መፈጠራቸውን ገልጸዋል። በቀጠይም በተወሰኑ የመንደር ማዕከላት የታየውን ሞዴልነት ወደ ሌሎች አካባቢዎች በማስፋት ህዝቡን ወደ ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤ የማሸጋገሩ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ርዕሰ መስተዳደሩ አስታውቀዋል። የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ቲቾት ኮመዳን በበኩላቸው ቀደም ሲል የአርሶና ከፊል አርብቶ አደሩ አሰፋፈር የተበታተነ በመሆኑ የግብርና ግብዓትና ሙያዊ ድጋፍ ለመስጠት አስቸጋሪ በመሆኑ የግብርና ልማቱ ሳይሻሻል መቆየቱን ተናግረዋል። ይሁን እንጂ የመንደር ማሰባሰብ መርሃ ግብሩ ከተካሄደ ወዲህ በተሰጠው የግብርና ቴክኖሎጂ የግብዓት አቅርቦትና ሙያዊ ድጋፍ የአርሶና ከፊል አርብቶ አደሩ ወደ ተሻለ የግብርና የአሰራር ዘይቤ እየተሸጋገረ መሆኑን ገልጸዋል። ቀደም ሲል ከግማሽ ሄክታር በማይበልጥ ማሳ ላይ ተወስኖ የነበረውም ከሁለት እስከ ሶስት ሄክታር መሬት ማልማት መጀመራቸውንም ጠቁመዋል። በአቦቦ ወረዳ በመንደር ከተሰባሰቡ መካከል ወይዘሮ አሪያት ኡጁሉ በሰጡት አስተያየት በመንደር መሰባሰባቸው የትምህርት፣  የጤና ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈ ወደ ተሻለ የግብርና ልማት ጭምር በመግባት ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ተናግረዋል። ''ከመንድር ማሰባሰበ ወዲህ ልጆቻችን እየተማሩ ነው፣ የሳር ጎጆ ቤታችንም በቆርቆሮ ቀይረናል ፣የጤና የውሃ አገልግሎትም ተሟልቶልናል ከመብራት በስተቀር '' ያሉት ደግሞ ሌለው ነዋሪ አርሶ አደር ሜድ ኡሞድ ናቸው። ሌላው የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ቻም ቻም አቡላ በሰጡት አስተያየት ''በመንድር ከመሰባሰባቸው በፊት በዓመት ሁለት ጊዜ ቀርቶ አንድ ጊዜም በአግባቡ አናመርትም ነበር'' ብለዋል። በመንደር ከተሰባሰቡ ወዲህ ግን ባገኙት ሙያዊ ድጋፍ በዓመት ሁለት ጊዜ በማምረት ኑሯቸውን ማሻሸል መቻላቸውን ተናግረዋል። በጋምቤላ ክልል ከ2003 ጀምሮ በተካሄደው የመንደር ማሰባሰበ መርሃ ግብር በ98 የመንደር ማዕከላት ከ40 ሺህ በላይ እማወራዎችና አባወራዎች መሰባሰባቸውን ከክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም