ብሔራዊ የስራ አውደ ርዕዩ የተማሪዎችን የስራ ፍለጋ እንግልት ይቀንሳል---ትምህርት ሚኒስቴር

74
አዲስ አበባ ነሃሴ 4/2010 ብሔራዊ የስራ አውደ ርዕይ ለአዲስ ተመራቂዎች መረጃ እንዲያገኙ በማድረግ ያለባቸውን የስራ ፍለጋ እንግልት እንደሚቀንስ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። የመጀመሪያው ብሄራዊ የስራ አውደ ርዕይ ዛሬ በሚሊኒየም አዳራሽ በይፋ ተጀምሯል። አውደ ርዕዩ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ስራ ቀጣሪዎች የሚያስፈልጋቸውን ብቁ የሰው ኃይል በአንድ ስፍራ ተገኝቶ ቅጥር የሚፈፅምበት ሲሆን ተማሪዎችም በተመረቁባቸው የትምህርት መስኮች ሊቀጥሯቸው የሚችሉ ተቋማትን በአንድ ላይ የሚያገኙበት ነው። አውደ ርዕዩን መርቀው የከፈቱት የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ እንደተናገሩት፤ ይህን መሰል መርሃግብር ማከናወን የስራ ፈላጊውንና ስራ ቀጣሪውን በአንድ ቦታ በማገናኘት በመካከላቸው ያለውን የመረጃ ክፍተት መሙላት ያስችላል። እስከ ዛሬ እንዲህ አይነት ስራ የሚፈለግበት ስልት ባለመኖሩ በቂ እውቀትና ችሎታ ያለው ተማሪ በመረጃ እጥረት ሳቢያ ቶሎ ስራ እንዳያገኝ አድርጓል። ይህ አውደ ርዕይ ይህን በስራ ፍለጋ ምክንያት በተማሪዎች ላይ የሚደርሰውን እንግልትና አላስፈላጊ ወጪ በመቀነስ ቶሎ ስራ እንዲያገኙ ያደርጋል ብለዋል። በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀው ከሚወጡ ተማሪዎች 80 በመቶ የሚሆኑትን በ12 ወራት ስራ ለማስያዝ 7 ስትራቴጂዎች ተቀርፀው እየተተገበሩ ሲሆን የስራ አውደ ርዕይ ማዘጋጀት አንዱ መሆኑንም ገልፀዋል። በዛሬው አውደ ርዕይ ከ30 ሺህ በላይ ተመራቂ ተማሪዎች ምዝገባ ያከናወኑ ሲሆን ከ150 በላይ ቀጣሪ ተቋማትም በአውደ ርዕዩ ተሳትፈዋል። በአውደ ርዕዩ ሁሉም መቀጠር ባይችሉም እንኳ ከአውደ ርዕዩ ቀድሞ ለተማሪዎች የሚሰጠው የስራ ዕድል መፍጠር ስልጠና ተማሪዎች ስራ መቀጠር የሚያስችላቸውን አቅም የሚሳድግላቸው እንደሆነም አስታውቀዋል። የሚጠበቀውን ያህል ተቋማት ተሳትፎ እንዳላደረጉ የጠቆሙት ሚኒስትሩ በቀጣይ የመንግስት ተቋማት በስፋት መሳተፍ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። 680 ሺህ ተማሪዎች በአገሪቱ ባሉ 46 ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ያሉ ሲሆን ተማሪዎቹ ወጥተው ስራ እንዲያገኙ ይህን መሰል አውደ ርዕዮች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ነው የገለፁት። በዚህ አመት 148 ሺህ ተማሪዎች በመጀመሪያ ዲግሪ ከግልና ከመንግስት ተቋማት ተመርቀው የወጡ ሲሆን 30 ሺህ ያህሉ ስራ አግኝተዋል። የ'ኢትዮ ጆብስ ዶት ኮም' ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ የሱፍ ረጃ በበኩላቸው ይህን አይነት አውደ ርዕይ ስራ ቀጣሪዎች ድርጅታቸውንና ያላቸውን የስራ ዕድል የሚያስተዋውቁበት አጋጣሚ የሚፈጥርላቸው እንደሆነ ገልጸዋል። የተመረቁ ተማሪዎችም የተለያዩ ድርጅቶችን በአንድ ቦታ የሚያገኙበት ስፍራ እንደሆነ ነው የገለጹት ። ጅግጅጋ፣ ጅማ፣ ሰመራና ወሎ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች የስራ ማዕከል በመክፈት ለመርሃ ግብሩ አስተዋፅኦ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል። ለፕሮግራሙ መሳካት ትምህርት ሚኒስቴር ትልቅ አስተዋዕኦ ማድረጉን የገለፁት የ'ደረጃ ዶት ኮም' ፕሮጀክት ማናጀርና የፕሮግራሙ አስተባባሪ ወይዘሪት ሲሃም አየለ ናቸው። በዛሬው የስራ አውደ ርዕይ የስራ ፈላጊውን ዝርዝር መረጃ (ሲቪ) ከተማሪዎች በመቀበል ምዝገባ እየተደረገ ነው፡፡ ኤም ብር ሁለት ሺህ ስራ ፈላጊዎችን ለመቅጠር እቅድ ያለው ሲሆን ለጊዜው 100 ተማሪዎችን ቅጥር እንደሚፈፅም አስታውቋል። በተመሳሳይ ሄኒከን ቢራ 40 ተማሪዎችን ለመቅጠር አስቦ ምዝገባ በማካሄድ ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። ዛሬ የተጀመረው የስራ አውደ ርዕይ ለሁለት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን ነገ ይጠናቀቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም