ሰብአዊ ድጋፉ በቂ እንዳልሆነ የጅግጅጋ ከተማ ተፈናቃዮች ገለጹ

74
ጂግጂጋ ነሀሴ 4/2010 የሚደረግላቸው ሰብአዊ ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ መቸገራቸውን በጅግጅጋ ከተማ ተፈጥሮ በነበረው ሁከት የተጎዱ ዜጎች ገለጹ፡፡ በከተማው ቀበሌ ስድስት በሚገኘው ቅዱስ ሜካኤል ቤተ ክርስቲያን ከተጠለሉ ተፈናቃዮች መካከል አቶ ወንድሙ ፍቅሩ እንዳሉት ባለፉት ቀናት በባለሀብቶች፣ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀልና በክልሉ መንግስት በኩል የመጠጥ ውሃና የምግብ እርዳታ እየቀረበላቸው ነው፡፡ ሆኖም አንድ ሊትር ውሃ ለአራት ሰዎች የሚከፋፈለውና ሌላውም ድጋፍ  በቂ ባለመሆኑ ለችግር መጋለጣቸውን ተናግረዋል፡፡ አቶ ፀጋ በለስ በበኩላቸው በቤተ እምነቱ የተጠለሉ ሰዎች እርዳታ እየቀረበላቸው ቢሆንም ቤታቸውና ንብረታቸውን የተዘረፉ ሰዎች እስካሁን ያገኙት ድጋፍ እንደሌለ  ገልጸዋል፡፡ ከችግሩ በኋላ የሚያረጋጋና የሚያወያይ  የመንግስት አካል ባለማግኘታቸው አሁንም በህዝቡ ውስጥ የደህንነት ስጋት በመፈጠሩ በርካታ ሰዎች ወደ ተለያዩ ከተሞች እየተሰደዱ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ተፈናቃዮቹ በተፈጠረው ረብሻ ህይወታቸውን ለማትረፍ በቤተ ክርስቲያንና መከላከያ ካምፕ ተጠልለው እንደሚገኙ  የተናገሩት ደግሞ የተጎጂዎች እርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴ አባል አቶ ወንዱሰን ተፈሪ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ የእርዳታ አስተባባሪ ዶክተር እዮብ መኮንን በበኩላቸው ለተጎጂዎች 500 ምንጣፍና ብርድ ልብስ ፣ለአራት ሺህ ሰዎች የሚያገለግል አልሚ ምግብና የህክምና እርዳታ መስጪያ ድንኳን በመትከል ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ማህበሩ የሚያቀርበው እርዳታ በቂ ባለመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት አፋጣኝ ድጋፍ  እንዲያደርጉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ የክልሉ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዲላሂ መሀሙድ እንዳሉት በችግሩ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች  የምግብ እርዳታ፣ የመኝታና  አልባሳት ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ተፈናቃዮች በክልሉ ጅግጅጋ፣ ጎዴ፣ዋርዴር፣ ቀብሪደሀርና  ደገህቡር ከተሞች  የሚገኙ ሲሆን የክልሉ መንግስት አስራ ስድስት ሚሊዮን ብር መድቦ  ሩዝ፣ፓስታ፣መካሮኒ፣ ዱቄት፣ዘይትና ስኳር በመግዛት እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከፌዴራል መንግስት የተላከ የእርዳታ እህልም  ቀርበው እየተከፋፈለ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በጎዴ ከተማ ተጎድተው የነበሩ ዜጎች በማህበረሰቡና በመንግስት ድጋፍ ወደየቤታቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በየቤታቸው የተጠለሉ ሰዎች እርዳታ ለማቅረብ ከፌዴራል፣ክልልና ከእምነት ተቋማትና ከተጎጂዎች የተውጣጡ አባላትን ያቀፈ ኮሚቴ ተቋቋሙ እየተሰራ መሆኑን የቢሮው ኃላፊ አመልክተዋል፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም