በምእራብ ወለጋ ዞን ከ121 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በዘመቻ ተተከለ

70
ጊምቢ ነሀሴ 4/2010 በምእራብ ወለጋ ዞን በዘንድሮው የክረምት ወቅት ከ121 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በዘመቻ መተከሉን የዞኑ  ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። በጽህፈት ቤቱ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ ሂደት ባለቤት አቶ ዳኜ ተሾመ እንዳስታወቁት እየጣለ ያለውን የክረምት ዝናብ በመጠቀም ችግኙ የተተከለው በዞኑ 20 ወረዳዎች በሚገኝ የተራቆተ አካባቢዎች ነው። ከሐምሌ መጀመሪያ አንስቶ ለ30 ቀናት በተካሄደው የችግኝ ተከላ ዘመቻ ከ100 ሺህ የሚበልጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል። የዞኑን የደን ሽፋን ለማሳደግና የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተተክሎ በመልማት ላይ ካለው ችግኝ መካከል የፍራፍሬ፣ የእንስሳት መኖ እንዲሁም ለአፈርና ውሃ እቀባ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ዝርያዎች ይገኙበታል። የተተከለው ችግኝ ጸድቆ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ለማድረግም አካባቢው ከሰውና እንስሳት ንክኪ ተከልሎ በህብረተሰቡ ጥበቃና እንክብካቤ እየተደረገለት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ባለሙያው እንዳሉት ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ሁኔታ ከተተከለው 227 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ውስጥ 85 በመቶ ጸድቋል። የጊምቢ ወረዳ መልካ ጋሲ ቀበሌ አርሶ አደር በቀለ አለሙ በሰጡት አስተያየት ባለፈው ዓመት በቀበሌያቸው የተተከለው የተለያየ የዛፍ ችግኝ ዛሬ ላይ ለምልሞ በማየታቸው ተደስተዋል። ዘንድሮም ልማቱን ለማጠናከር በራሳቸው ተነሳሽነት በችግኝ ተከላው መሳተፋቸውን የሚናገሩት አርሶ አደሩ ይህም የአከባቢያቸው ልምላሜ እንዲጨምር አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልፀዋል፡፡ ሌላኛው የነጆ ወረዳ በሪዮ በዴሶ ቀበሌ አስተያየት ሰጪ አርሶ አደር አበበ ታሲሳ በበኩላቸው የቤተሰብ ጉልበት በመጠቀም በግል ይዞታቸው ላይ የእንስሳት መኖና የፍራፍሬ ችግኝ ተክለው እያለሙ  መሆናቸውን ተናግረዋል። በየዓመቱ የሚተክሉት የዛፍ ዝርያም የእርሻ ማሳቸውን ከጎርፍና ከደለል በመታደግ ለሰብል ምርታማነት አስተዋጽኦ ማድርጉንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም