አሸባሪውን በስሙ አለመጥራት ለምን?

132

በኢዜአ ሪፖርተር

• ተበአስ በእንተ ጽድቅ እስከ ለሞት

"አንድ ጣት ቁንጫ አይገድልም" ይባላል። እውነትም አንድ ጣት ጥንካሬዋ እንዳለ ሆኖ ብቻዋን ትንሿን ቁንጫ እንኳን የመግደል አቅሙም ችሎታውም የላትም።

"ድር ቢያብር አንበሳ ያስር" ነውና ነገሩ ለውጤት ህብረትና አንድነት በእጅግ ወሳኝ ነው። ሁለት ጣቶች ተአምር ለመስራት እንደሚችሉት ሁሉ ህብረት ወሳኝ የመሆኑ ጉዳይ አያጠያይቅም።

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ አሁን ላይ የውስጥና የውጭ አደጋ ተጋርጦባታል። "እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል" ብሎ ቆርጦ የተነሳው አሸባሪው ህወሃት ህፃናትን ለጦርነት እያሰለፈ የጥፋት ቡድኑ ቱባዎችን በደም ጡረታ ለማኖር እያመቻቸ ይገኛል።

ይህ ትልማቸው እንደ ጉም በኖ እንደሚጠፋ ለአገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ግልፅ ነው። የራሳቸውን ልጆችና ቤተሰቦች አንደላቀው አውሮፓና አሜሪካ እያስተማሩ የደሃ ልጅ ሞት እየተፈረደበት የአሸባሪው ህወሃት የእሳት እራት ሆኖ አይቀጥልም።

የኢትዮጵያንና የህዝቦቿን ጠንቅ አሸባሪ ሃይል ለማጥፋት ህዝቦቿ ከጫፍ ጫፍ ተነስተዋል። ከወልዲያ እስከ ሃዲያ፣ ከአሳኢታ እስከ ወላይታና ከምባታ፣ ከጉሙዝ እስከ መንዝ፣ ከጋምቤላ አስከ ዲላ፣ ከጎንደር እስከ ጉደር፣ ከአማሮ ኬሌ እስከ ሞያሌ፣ ከመተማ እስከ ጅማ፣ ከቀብሪ ደሃር እስከ ባህር ዳር፣ ከመሃል ሸገር እስከ ዳር አገር ሴት ወንዱ፣ ወጣት አዛውንቱ ለአገሩ ህልውና ነፍጥ አንግቶ የድል ችቦ ለመለኮስ ተዘጋጅቷል።

የአገር ህልውና ዘመቻውን ኢትዮጵያዊያን በድል እንደሚያጠናቅቁትም ጥርጥር የለውም። ምክንያቱም ፍልሚያው አገር ለማፍረስ በተነሳ ቡድን እና አገር ለማዳን በተነሳ ህዝብ መካከል ነውና።

“የትውልድ ጉልበቱ ሕብረቱ፤ የህዝብ ሀብቱ አንድነቱ” በመሆኑ የአሸባሪው ህወሃት እጣ ፈንታ 'ዞሮ ዞሮ ከቤት፣ ኖሮ ኖሮ ከመሬት' እንደሚባለው መሆኑ አይቀርም። "ተበአስ በእንተ ጽድቅ እስከ ለሞት" ይላል ግዕዙ፤ ትርጉሙም "ለእውነት እስከ ሞት ድረስ ተፋለም" መሆኑን ሊቆቹ ይናገራሉ። ኢትዮጵያዊያን እውነትን ይዘው ካሃዲውን ለመፋለም ተዘጋጅተዋል። "ነገረኛ ሰው ከቤቱ አይሞትም" ነውና ነገሩ አሸባሪው ህወሃትም ከቤቱ ወጥቶ ወደ መቃብሩ በማምራት ላይ ይገኛል።

አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን በተቆጣጠረባቸው ዓመታት በህገ መንግስቱ እየማለ ዘርፏል፤ ጥያቄ የሚያነሱበትን በይፋም በስውርም እየገደለ ቀብሯል። በጥቅሙ ለመጣበት ማንኛውም አካል ዘመድ ወዳጅ ሳይል ጭምር ከመግደልና ማኮላሸት ወደ ኋላ ሳይል ዓመታትን አሳልፏል። አፈጣጠሩ ከጫካ ጀምሮ ለእውነት የሚታገሉትን ጓዶቹን ጭምር በግልፅ "ከአጠገቤ እራቁ" በማለት ወደ ሌሎች አገሮች ሲሸኝ "እምቢ አሻፈረኝ" የሚል ሲያጋጥመው ደግሞ በተጠና አሻጥር መግደል እንደሚያውቅበት የአደባባይ ምስጢር ነው። አሸባሪው ህወሃት ከአመሰራረቱም ጀምሮ የመጨረሻ ግብ አድርጎ የቀመረው እስከቻለ ድረስ ዘርፎ ሲያቅተው ኢትዮጵያን ብዙ አገር የማድርግ የረጅም ጊዜ እቅድ መሆኑ እርግጥ ነበር። ይሁን እንጂ ጆርጅ ቦልተን እንዳለው "ኢትዮጵያ ዩጎዛላቪያ አይደለችም፤ አልፈረሰችም፤ ወደ ፊትም አትፈርስም፤ እናፈርሳለን የሚሉ ሁሉ ቢፈርሱ እንጂ" የኢትዮጵያዊያን የጋራ ቤት ሆና ትቀጥላለች። 

የአሸባሪው ህወሃት ሴራ ከሽፎ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያጠመደው "ፈንጅ" ለውጡ ባመጣቸው አገር ወዳዶችና በህዝቡ ትብብር ቀስ በቀስ እየመከነ ይገኛል። ህዝብ እየገነባው የነበረውን የኢትዮጵያን ታላቁ ህዳሴ ግድብ አሸባሪው ህወሃት ከውጭ ሃይሎች ጋር ተመሳጥሮ "እጀ ሰባራ" በማድርግ ግድቡን "ሊያጨነግፈው" ብዙ ተጉዞ እንደነበር አገር ያወቀው ጉዳይ ነው። ይህም ሆኖ በለውጡ ሃይል ማስተካከያ ተደርጎበት ለሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በቅቷል።

አሸባሪው ሃይል ግንባታው እንዲሰናከል ከውጭ ሃይሎች ቀድሞ ቀብድ የተቀበለበት ግድብ በለውጡ አመራር ማስተካከያ እየተደረገበት መሆኑን ሲያረጋግጥ በአፈ ቀላጤው ጌታቸው ረዳ በኩል "ግድቡ ተሸጧል" የሚል ነጠላ ዜማ በማውጣት ለማቀንቀን ቢሞክርም ተቀባይ አጥቶ እውነታውም ተገልጧል። 

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት ከሃዲውንና አሸባሪው ህወሃትን አስቆጭቶ፤ ግንባታው "የህልም እንጀራ ነው" ይሉ የነበሩትን ግብፅና ሱዳንንም አበሳጭቷል። የሰረቀውን አንጠልጥሎ ትግራይ የከተመው የአሸባሪው ህወሃት "እድፉን በውሃ፣ በደሉን በንስሃ" ማከም ሲገባው ይባስ ብሎ የሰሜን እዝ የአገር መከላከያ ሰራዊትን በድንገት በማጥቃት የአደባባይ ክህደት ፈፀመ።

ከዚህ በኋላ ጁንታው ኢትዮጵያን ዳግም በመቆጣጠር ወደ መንበረ ስልጣን ለመመለስ የነበረው እቅድ ከሽፎ እግር በእግር ተሳዶ "አፈር ነህና ....” እንደሚባለው መነሻውም መድረሻውም ደደቢት ሆነ፤ የሽር ሽር ቦታውም ቆላ ተንቤን" ሆኖ ከረመ።

የአሸባሪው ህወሃት ሃይል "የቋጥኝ አይጥ" ሆኖ በአገር መከላከያ ሰራዊት ሲታደን ከርሞ ለትግራይ ህዝብ ጥሞና ሲል ሰራዊቱ ለቆ ሲወጣ "እንደ ክረምት አግቢ" ተበትኖ የከረመው ቡድን ተሰባስቦ በውጭ አዝማቾቹ አይዞህ ባይነት "ኢትዮጵያን እስከ ሲኦል ገብተን እናፈርሳለን" በሚል ወደ ጦርነት ገብቷል። 

የተለያዩ የውጭ ሃይሎች በኢትዮጵያዊያን ትግል የሞተውን የህወሃት "ጭንጋፍ" ጠጋግነውና ደጋግፈው ወደ አራት ኪሎ ለመመለስ ጥረታቸውን ቀጥለዋል። "ህልም አይከለከል" እንደተባለው የኢትዮጵያ ጠላቶች ተኝተው ቢያልሙም "ቅዥት" ከማለት ውጭ ለፍች የሚቀርብ ትክክለኛ ህልም አለመሆኑን እንዲያረጋግጡ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያን በማፍረስ ከጉባ የሚለኮሰውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ የብልፅግና ችቦ ለማጥፋት የሚያደርጉት ጥረት ከንቱ ልፋት እንጂ በጭራሽ የሚሳካ አይሆንም። በአሜሪካ የባይደን አስተዳደርና አጋሮቿም "እምቢ ለአገሬ" ብሎ የሚሰራን መንግስት በሌላ ተላላኪ ሃይል ለመቀየር የሚያደርጉት ጥረት ፈፅሞ አይሳካም። "ጥሩ አማጭን መጦር፤ መጥፎ አማጭን በጦር" ነውና ነገሩ ኢትዮጵያዊያን መሪያቸውን በመረጡበት ማግስት መጥፎ አማጩን እየረገሙ አሸባሪው ህወሃትን ለመፋለም ጦራቸውን ሰብቀዋል።

መጥፎ አማጮች በኢትዮጵያ አሸባሪ የተባለን ሃይል በስሙ ጠርተው ከማውገዝ ይልቅ ሸምጋይ መስለው ለመቅረብ እየሞከሩ ነው። እነርሱ አሸባሪ ያሉትን ዓለም በስሙ ጠርቶ እንዲያወግዘው ብሎም እንዲዋጋው እየሰበኩ፣ ባህር አቋርጠው በመሻገር ከምድረ ገጽ ሲያጠፉ የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት በአንድ ምሽት በድንገት ክህደት ፈፅሞ ስብዕናቸውን ነክቶ ሞታቸውንም አርክሶ ግፍ የፈፀመን ሃይል "አሸባሪ" ብሎ ለመጥራትና የሚገባውን ቦታ ለመስጠት አለመድፈራቸው ለምን ይሆን? የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀሬ ነው። ጥያቄው ቢነሳም እነርሱ ለሚመቻቸው እንደሚያደሉ፣ ተንከባክበው እንደሚጓዙ የሚስት አይኖርም፤ እየሆነ ያለውም ይሄው ነው።

አሸባሪው ህወሃት አሁንም የትግራይን ወሰን አልፎ በአማራ እና አፋር ክልሎች ንፁሃንን አፈናቅሎ ለችግርና እንግልት እየዳረገ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማውገዝ አልደፈረም፤ አልሞከረምም። በትግራይም፣ በአፋርም ይሁን አማራ ዜጎች እየተፈናቀሉ ለችግርና ስቃይ መዳረጋቸው ማንንም አገር ወዳድ ዜጋ የሚያስደስት አይሆንም፤ ችግሩም የጋራ መሆኑ እርግጥ ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን የአሸባሪው ህወሃት ሃይል የጥፋትና አገር የመበተን ውጥን በማክሸፍ ታግሎ ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል። 

“የትውልድ ጉልበቱ ህብረቱ፤ የህዝብ ሀብቱ አንድነቱ” በመሆኑ ኢትዮጵያን ለማፍረስ “ሲኦል እገባለሁ” ያለውን የአሸባሪው ህወሃት ቡድን ሲኦል ለማስገባት በጋራ መቆም ይገባል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም