የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና ሠራተኞች ደም ለገሱ

1086

ነሀሴ 04/2013  (ኢዜአ) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁ የምክር ቤት አባላትና ሠራተኞች ለመከላከያ ሠራዊት ደም ለግስዋል።
በደም ልገሳው መርሃ ግብር ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ጨምሮ የሥራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁ የምክር ቤቱ አባላትና ሰራተኞች ተገኝተዋል።

በዚህ ወቅት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤ የደም ልገሳው የአገር ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የህይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ላለው  “የአገር መከላከያ ሰራዊት ደጀንነታችንን ለማሳየት ነው” ብለዋል።

የምክር ቤቱ ሰራተኞችና የስራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁ አባላት ከደም ልገሳው በተጨማሪ የአንድ ወር ደመወዛቸው ለመስጠት መወሰናቸውን አቶ ታገሰ ተናግረዋል።

የምክር ቤቱ የሴቶች ኮከስ አደረጃጀት ለሠራዊቱ የስንቅ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረው፤ ግንባር ድረስ ሄደው አሸባሪውን የህወሃት ቡድን ለመመከት ጥያቄ ያቀረቡ የምክር ቤቱ ሰራተኞች እንዳሉም ገልጸዋል።