ላልተቆራረጠ የሕክምና ግብአት አቅርቦት መንግስት በትኩረት እየሠራ ነው…ጤና ሚኒስቴር

1096

አርባ ምንጭ ነሐሴ 02/2013 (ኢዜአ)  ያልተቆራረጠ የሕክምና ግብአቶች አቅርቦት እንዲኖር መንግስት በትኩረት እየሠራ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።

በአቅርቦት ስርአቱ ዘመኑን ታሳቢ ያደረገ ምላሽ ለመስጠት የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ እንዲያደርግም ተመላክቷል።

ሚኒስትሯ በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሄደ ባለው 4ኛው አገር አቀፍ የመድሃኒት አቅርቦት ዓመታዊ የምክክር መድረክ ላይ እንዳሉት ለጤና ስርአት መሻሻል የህክምና ግብአት አቅርቦት ወሳኝ ሚና አለው።

በመሆኑም የጤና መርሃግብሮችንና አገልግሎቶችን ከማስፋትና ተደራሽ ከማድረግ ጎን ለጎን ያልተቆራረጠ የህክምና ግብአቶች አቅርቦት እንዲኖር መንግስት በትኩረት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የግዥ ስርአት፣ የግብአት ክምችትና ስርጭት አሠራርን በማዘመን የተቀናጀ የመድሃኒት አስተዳደር ስርአት መዘርጋቱን ነው የገለጹት።

“ይህም ለጤናው ዘርፍ ስኬት ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጓል” ብለዋል።

ዶክተር ሊያ እንዳሉት ሀገሪቱ ከውስጥና ከውጭ እየገጠማት ባለው ፈተና እንዲሁም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳንበገር በግብአት አቅርቦት በኩል የተሻለ ተግባራትን አከናውናለች።

በቀጣይም በአቅርቦት ስርአቱ ዘመኑ በሚጠይቀው ልክ ምላሽ ለመስጠትና ለተገልጋዩ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ማድረግ እንዳለበት ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ በበኩላቸው “ለጤናው ዘርፍ ውጤታማነት የሰው ሃይልና መሠረተ ልማት ወሳኝ ናቸው” ብለዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ የሕክምና ግብአቶች መሟላት አስፈላጊ መሆኑንና ለዚህም ኤጀንሲው የድርሻውን ሲወጣ መቆየቱን አመልክተዋል፡፡

ዳይሬክተሩ እንዳሉት ኤጀንሲው ፈዋሽነታቸውና ደህንነታቸው የተረጋገጠ መድሃኒቶችና የህክምና መገልገያ መሣሪያዎችን በበቂ ሁኔታና በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ይገኛል፡፡

“በበጀት ዓመቱ ከ27 ቢሊዮን 613 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ መድሃኒቶች፣ ኬሚካሎችና የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎችን ማሠራጨት ተችሏል” ሲሉም አክለዋል፡፡

የግዥ ሂደቱ ቀልጣፋ እንዲሆን ከኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን፣ ከባንክ፣ ከኢንሹራንስ፣ ከኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ድርጅት፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከኢትዮጵያ ጉሙሩክ ኮሚሽንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ለሁለት ቀናት በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ የኤጀንሲው የ2013 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ተገምግሟል።

በመድረኩም የጤና ሚኒስቴር ሃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የኤጀንሲው ከፍተኛ አመራሮች፣ በክልሎች ያሉ ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው አካለት ተገኝተዋል።