በመዲናዋ የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ በሰላም ተጠናቋል

1324

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2013(ኢዜአ) በመዲናዋ የአሸባሪው ህወሃት ቡድንን ለማውገዝና የመከላከያ ሰራዊቱን ለመደገፍ የተካሄደው ሰልፍ በሰላም መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ።

”ኢትዮጵያን ለማዳን እዘምታለሁ የትም፣ መቼም፣ በምንም” በሚል መሪ ሃሳብ በመስቀል አደባባይ በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ የአዲስ አበባና በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

በሰልፉ የመከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ እያከናወነ ያለውን ተግባር የሚደግፉና የአሸባሪውን የህወሃት ቡድን የጥፋት እንቅስቃሴ የሚቃወሙ መልእክቶች ተላልፈዋል።

በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በሰልፉ የተሳተፉ ሲሆን፤ ሰልፉ በሰላማዊ መንገድ ተካሄዶ መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ሰልፉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የመዲናዋ ነዋሪዎችና የሰልፉ ተሳታፊዎች ላደረጉት አስተዋጽኦም ኮሚሽኑ ምስጋና አቅርቧል።

በተጨማሪ ሰልፉን ለአስተባበሩና ለመሩ አካላት ምስጋና ያቀረበ ሲሆን፤ ኮሚሽኑ ሕብረተሰቡ የመዲናዋን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ  እያደረገ ያለውን ትብብር አድንቋል።

የጸጥታ ኃይል አባላት የመዲናዋን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ መሆኑንም ኮሚሽኑ ገልጿለ።

ሕብረተሰቡ የከተማዋን ፀጥታ አስተማማኝ ለማድረግ በሚካሔዱ ተግባራት ላይ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።