ዘመቻውን በድል አጠናቀን ልማታችንን እናስቀጥላለን --- የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል

71

ጅማ፣ነሐሴ 01 ቀን 2013 (ኢዜአ) ሀገር የማዳንና የህልውና ዘመቻን በድል አጠናቀን ልማታችንን እናስቀጥላለን ሲሉ የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ተናገሩ።

ጅማ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ሙያዎች ያሰለጠናቸውን 3ሺ 927 ተማሪዎችን በመጀመሪያ ፣ ሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ዛሬ አስመርቋል።

በምረቃው ስነ-ስርዓት በክብር እንግድነት የተገኙት የሰላም ሚኒስትሯ እንዳሉት፤ትምህርት የእድገት መሰረት በመሆኑ ተመራቂዎችም ራሳቸውን በእውቀት ለማሻሻልና ለመለወጥ መስራት ይጠበቅባቸዋል።

ኢትዮጵያ በርካታ የልማትና የግንኙነት ለውጦችን ማምጣት መቻሏን ለአለም ማሳየቷን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ሀገር የማዳን የህልውና ዘመቻም በድል አጠናቀን ልማታችንን እናስቀጥላለን ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በለውጡ ሂደት ውስጥ ችግሮችን በሰላም ለመፍታት ያደረገችው ጥረት መላው ኢትዮጵያውያን የሚያውቁት በመሆኑ የተጀመረው ዘመቻ ሁላችንም አንድ ሆነን በድል እንወጣዋለን ብለዋል።

ሌላው የስነ-ስርዓቱ ተካፋይ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በበኩላቸው፤ ተመራቂዎች ሀገሪቱን ወደተሻለ ደረጃ የማሻገር ተስፋ እንደተጣለባቸው ተናግረዋል።

በየቀኑ በመማር ሀገራችሁን የመቀየር ሀላፊነት በእጃችሁ ስለሆነ ተግታችሁ የለውጥ ፈጣሪ እንድትሆኑ አደራ አለባችሁም ብለዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀማል አባ ፊጣ፤ ተማሪዎቹ ተቋሙ በምርምር፣ በአመራርና ቴክኖሎጂ በሀገር አቀፍ ደረጃ አንደኛ በወጣበት ማግስት መመረቃቸው ከወትሮው የተለየ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

የኮሮናን ተፅዕኖ ተቋቁመው ለዚህ የበቁት ተማሪዎችና ወላጆች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክትም አስተላልፈዋል።

ከአጠቃላይ ተመራቂዎች ውስጥ 403 በሁለተኛ እና 18 በሶስተኛ ዲግሪ ሲሆን ቀሪዎቹ በመጀመሪያ ዲግሪ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ሪጅስትራር ዋና ዳይሬክተር አቶ ብሩክ ሀይለሚካኤል ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም