የሀገሪቱ ዓመታዊ የግብርና ምርታማነት ወደ 302 ሚሊዮን ኩንታል አደገ

1310

ሀዋሳ ፤ ሐምሌ 30/2013 (ኢዜአ) የሀገሪቱ ዓመታዊ የግብርና ምርታማነት ከ270 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 302 ሚሊዮን ኩንታል ማደጉ ተገለጸ።
የግብርና ሚኒስቴር እና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና፣አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ቋሚ ኮሚቴ የአምስተኛው ዙር ምርጫ ዘመን የዘርፉን አጠቃላይ የስራ አፈጻጸም  የምክክር መድራክ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ  ተካሄዷል።

በመድረኩም ባለፉት ስድሰት ዓመታት ቋሚ ኮሚቴው በግብርና ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት በክትትል፣ በቁጥጥርና በድጋፍ ዙሪያ ያከናወኗቸው ጥቅል የሰነድ ሪፖርት ቀርቧል።

በነዚህ ጊዜያት በግብርና ዘርፍ ከተገኙ ስኬቶች መካከል ዓመታዊ የግብርና ምርታማነት ከ270 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 302 ሚሊዮን ኩንታል ማደጉ ተጠቅሷል።

የውጭ ምንዛሪ ግኝት ውስጥ 80 በመቶ ከግብርና ምርቶች መሆኑም  በሰነድ ሪፖርቱ ተመላክቷል።

አርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ ከተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ጋር በቅንጀት ለመስራት በተደረገው ጥረት ውጤት ማስገኘቱም ተገልጿል።

በቀጣይ ትኩረት ከሚሹ ጉዳዮች መካከል የምርምር ማዕከላት የመሬት ይዞታ አለመከበር፣በቂ የምርምር ቦታ አለማግኘትና የነባር ምርምር ማዕከላት በተለያዩ አካላት መነጠቅና ምርምሮች መቋረጥን ተጠቅሷል።

የሰብል በሽታና ተባይ ለመከላከል፣የአፈር አሲዳማነትን የሚቋቋሙ ዝርያዎችን ማውጣት እና አካባቢ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ መጤና ተዛማጅ ዕጸዋቶችን ለመከላከል የሚያስችሉ ብቃት ያላቸውን ውጤታማ ቴክኖሎጂዎችን ለአምራቹ ለማቅረብ  እየተሰራ ያለው ስራ በተገቢ  መንገድ ለማስቀጠል  የክትትልና የቁጥጥር ስራው  ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴው  በቀጣይ ትኩረት ከሚሹ ጉዳዮች አካቷል።

የቀረበውን ሪፖርት በጋራ በመገምገምና በማፅደቅ በቀጣይ አዲስ ለሚመጣው ቋሚ ኮሚቴ መነሻ ሰነድ ሆኖ እንዲያገለግል ታስቦ  የምክከር መድረኩ መዘጋጀቱን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ አልማዝ መሰለ አስረድተዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲ በበኩላቸው፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት በተለይ ከለውጡ ወዲህ ግብርናው ወደ መዋቅራዊ ሽግግር /ትራንስፎርሜሽን/ ሊያመራ  እንደሚችል መሠረታዊ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ለዚህ እውን መሆን ቋሚ ኮሚቴው በተለይ በፖሊሲ ረገድ ማነቆ የሆኑ ጉዳዮች አሳታፊ በሆነ መንገድ ተለይተው እንዲፈቱ ከፍተኛ ድጋፍ በማድረጉ ለግብርና መዘመንና እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አውሰተዋል።

በዚህም መሠረታዊ የሆኑ የህግ ፣የአዋጅ፣ ደንብና የአሰራር ክፍተቶችን ለመዝጋት የሚያስችሉ ስራዎች መከናወኑን ጠቁመዋል።

በተለይ መሠረታዊ የሆኑ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና ጥራትን ለማሻሻል የሚያስችሉ ግብዓቶች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ መወሰኑ የአርሶ አደሩ ምርታማነትን በማሳደግ ትልቅ እምርታ ያመጣል ብለን እንጠብቃለን ብለዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የፌዴራል ኀብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ስሩር ፤በቋሚ ኮሚቴው የቀረበው ሰነድ ግብርናን ለማዘመንና ውጤታማ ለማድረግ ሲሰሩ የቆዩ ስራዎችን ጠንካራና ደካማ ጎኖችን አንጥሮ የሚያሳይ በመሆኑ ለቀጣይ ስራችን ጉልበት ይሆናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ድሪባ ገለቴ በበኩላቸው፤ ቋሚ ኮሚቴው ከተቋማቸው ጋር በቅርበት በመስራትና የምርምሩን ውስጣዊ ሁኔታ በመረዳት  አስፈላጊው ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

የቀረበው የሰነድ ሪፖርቱ እንዳመለከተው ፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና፣አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ቋሚ ኮሚቴ በስድሰት ዓመቱ ውስጥ  81 ጊዜ በአስፈፃሚ  አካላት ላይ የአካል ግምገማ በማድረግ ደግፏል።