በመዲናዋ የትራፊክ ደንብ የሚተላለፉ አሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር አዲስ ቴክኖሎጂ ከቀጣዩ ዓመት ስራ ላይ ይውላል ይገባል

133
አዲስ አበባ ነሀሴ 3/2010 በመዲናዋ የትራፊክ ደንብ የሚተላለፉ አሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችል የሞባይል አፕሊኬሽን አገልግሎት ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ ወደ ስራ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ አስታወቀ። አገልግሎቱ የትራፊክ አደጋ መረጃ አያያዝና ሪፖርት ማሻሻልን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነም ገልጿል። የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጅሬኛ ሂርጳ ለኢዜአ እንደገለጹት አገልግሎቱ 'ፖይንት ፔናሊቲ ስኮር' የሚል ስያሜ እንዳለውና ዋነኛ ዓላማውም የትራፊክ ደንብ በሚተላለፉ አሽከርካሪዎች ላይ ቁጥጥር ለማድረግ ነው። በሞባይል አፕሊኬሽኑ ላይ የአሽከርካሪው ስም፣ መንጃ ፈቃድ፣ ስለ ጥፋቱና የጥፋት እርከኑ እንዲሁም የአሽከርካሪውን ምስልና 'ጂፔ ኤስ'ን ያካተተ እንደሆነም ተናግረዋል። በሞባይል አፕሌኬሽኑ ላይ የተመዘገበው መረጃ በኢንተርኔት አማካኝነት በኤጀንሲው ከሚገኘው ዋናው የመረጃ ቋት ጋር የሚገናኝ እንደሆነም ጠቅሰዋል። አሽከርካሪው በሌላ ወቅት የትራፊክ ደንብ በሚተላለፍበት ወቅት በሞባይል አፕሊኬሽኑ ላይ ያለው የአሽከርካሪው መረጃ ከዚህ በፊት ጥፋት መፈጸሙን የሚያሳይ መረጃ ስላለ በደንቡ በተደራራቢ ጥፋት እርምጃ እንደሚወሰድበትም አመልክተዋል። ህግና ስርአትን የማያከብሩ እና ተደጋጋሚ ጥፋት የሚያጠፉ አሽከርካሪዎችን ከመንገድ ለማውጣት በሚደረገው ጥረትም አፕሊኬሽኑ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ብለዋል። ፖይንት ፔናሊቲ የሚባለውን የሞባይል አፕሊኬሽን አገልግሎት 'ከስተር ኮምፒዩተር ሶሉሽን' የተባለ አገር አቀፍ ተቋም እንዳዘጋጀው ነው አቶ ጅሬኛ የጠቆሙት።   እስካሁን በ100 ስልኮች ላይ አፕሊኬሽኑ እንደተጫነና እፕሊኬሽኑ የተጫነበት 100 ስልኮች ለትራፊክ ፖሊሶች እንደተሰጡም አስረድተዋል።   ለትራፊክ ፖሊሶቹም ስለ አገልግሎቱ አሰጣጥ ስልጠና እንደተሰጠም በመግለጽ።   የሞባይል አፕሊኬሽን አገልግሎቱን በፓይለት ደረጃ በተወሰኑ አካባቢዎች ተግባራዊ ለማድረግ እንደተሞከረና በዚያም ወቅት የሲስተም አለመስራት ችግር እንዳገጠመ ተናግረዋል።   ችግሩን በባለሙያዎች የመፍታት ስራ እየተጠናቀቀ መሆኑንና በአጠቃላይ አገልግሎቱ በ2011 ዓ.ም እንደሚጀመር አስታውቀዋል።   እስካሁን ለሞባይል አፕሊኬሽኑ አገልግሎትና የሲስተም ዝርጋትው 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ጠቅሰዋል።   በቀጣዩ ዓመት ወደ ስራ የሚገባው አገልግሎቱ የኤጀንሲውን የትራፊክ አደጋ መረጃ አያያዝና ሪፖርት ማሻሻልን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም