በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ጾታዊ ጥቃት ለመከላከል የተጠናከረ ቅንጅት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

4049

አክሱም ግንቦት 8/2010 በትግራይ ክልል በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ጾታዊ፣አካላዊና ስነ አእምራዊ ጥቃት ለመከላከል ጠንካራ ቅንጅት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ፡፡

በአክሱም ከተማ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየውን  ክልል አቀፍ  የሴቶች ኮንፍረንስ  ትላንት ተጠናቋል፡፡

የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አረጋይ ገብረእግዚአብሔር በኮንፍረንሱ ወቅት  እንዳሉት የሴቶች መብት ለማስከበርና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የወጣው  ህግና ፖለሲ ወደ ተግባር ለማሸጋገር ብዙ መስራት ይጠይቃል፡፡

ሴቶች ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶችን ለመከለከል እስካሁን የተደረገው ጥረት እምብዛም ለውጥ እንዳላመጣ ነው የተናገሩት፡፡

በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 715 ሴቶችና ህጻናት ላይ የተለያዩ ጾታዊ ጥቃቶች እንደደረሳባቸው ጠቅሰው፤ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ጭማሪ ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡

“ሴቶች በተደራጀ መልኩ ትግላቸው ከማጠናከር ባለፈ ህብረተሰብ አቀፍ የግንዘቤ ማስጨበጫ ስራዎች መሰራት አለበት” ብለዋል፡፡

አጥፊዎች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ የሴቶች ማህበር የማይቋረጥ ትግል ማድረግ እንዳለበት ያመለከቱት ደግሞ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ዶክተር ፋና ሀጎስ ናቸው፡፡

በሴቶችና ህጸናት ጥቃት በሚያደርሱት ላይ ተገቢውን የህግ ቅጣት እንዲያገኙ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ  ልዩ ችሎት መሰየሙን ፕሬዝዳንቷ ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ሴቶች ማህበር ሊቀመንበር ወይዘሮ ዘነበች ፍስሃ በበኩላቸው በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በመለየትና መረጃ በመስጠት ፈጣን ውሳኔ እንዲሰጥ የህብረተሰቡ ትብብር መኖር እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

“እስካሁን ጥቃቱን መከላከል ያልተቻለው  የሴቶች ማህበር ጠንካራ ትግል ባለማድረጉ ነው” ብለዋል፡፡

ጥቃቱን ለማስቆም ሴቶች በማህበራቸው የነቃ ተሳትፎ በማድረግ እንዲታገሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በክልሉ በሴቶችና ህጻናት ላይ እየደረሰ ያለውን ጾታዊ፣አካላዊና ስነ አእምራዊ  ጥቃት ለመከላከል ሰፊ ጥረትና ጠንካራ ቅንጅት እንደሚያስፈልግ የኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች በሰጡት አሰተያየት ገልጸዋል፡፡