ምእራባውያን ለኢትዮጵያ ያዘጋጁት ስውር ሴራ

158

የጂኦ ፖለቲክስ ፕሬስ ትንተና

ጂኦ ፖለቲክስ ፕሬስ ዓለማቀፋዊ የሆኑ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን መሰረት ያደረጉ ትንታኔዎችን ይሰራል። ይህ ገጽ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ሰፋ ያለ ትንታኔ አስነብቧል። ጂኦ ፖለቲክስ “From Basma to Ethiopia – How C2FC is Using Lethal Journalism to Conduct Information Warfare and Lawfare against Ethiopia”  በሚል ርእስ ባወጣው ጽሑፍ ምእራባውያን በትግራይ ክልል የተካሄደውን ህግ የማስከበር እርምጃ ተከትሎ የያዙት ስውር አጀንዳ በኢትዮጵያ ደካማ መንግስት እንዲኖር ማድረግ አሊያም የመንግስት ለውጥ ማድረግ መሆኑን አስፍሯል።

ሶሪያ የፈረሰችው ምእራባውያኑ ሀገራት “ባስማ” በሚል ስያሜ ባዘጋጁት ፕሮጀክት መሆኑን የሚጠቁመው የጂኦ ፖለቲክስ ትንታኔ ለኢትዮጵያ ደግሞ ትእዛዝ መስጫና መቆጣጠሪያ ማእከል “Command and Control Fusion Center (C2FC)” የሚል ፕሮጀክት መንደፋቸውን አመልክቷል። ይህ ፕሮጀክት ኢትዮጵያን እስከመጨረሻ የመበታተን ደረጃ የሚያደርስ ፕሮጀክት እንደሆነም ጠቁሟል።

በሶሪያ የተቀረጸው ባስማ ፕሮጀክት የደህንነት መረጃዎችን በአግባቡ ሰብስቦና ተንትኖ የሚያቀርብ ሲሆን በእርዳታ ስም በምእራባውያኑ ሀገራት የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች አማካኝነት ሶሪያን ለማፍረስ የተተገበረ ፕሮጀክት መሆኑን ጂኦ ፖለቲክስ አስነብቧል። ፕሮጀክቱ ሶሪያ አሁን ወዳለችበት የተፈረካከሰች ሀገር ወደ መሆን ደረጃ አድርሷታል። ምእራባውያን ይህን ፕሮጀክት የጀመሩት "በጦርነት የተጎዱ ሶርያውያን የእርዳታ እህል ማግኘት አለባቸው” በሚል እንደነበር  የሚጠቁመው ጽሑፉ ጉዳዩ  እያደገ  መጥቶ የመንግስት ለውጥ ያስፈልጋል ወደ ሚል መሸጋገሩን አንስቷል።

ልክ እንደባስማ ፕሮጀክት ሁሉ በኢትዮጵያ ተመሳሳይ ዘመቻ መክፈታቸውን  ያመለከተው የጂኦ ፖለቲክስ ትንታኔ ፤ የህወሓት ቡድን በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ የአውሮፓ ህብረት ባለስልጣናት በፈረንጆቹ ኖቨምበር 10 ቀን 2020 የኢትዮጵያ መንግስት ሊዳከም በሚችልበት ሁኔታ ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውንና ባለ 7 ገጽ ሪፖርት ማዘጋጀታቸውን ጽሑፉ ያብራራል።  የባለ7 ገጽ የሪፖርት ሰነድ ከህብረቱ አባላት በጥንቃቄ ለተመረጡ ቡድኖች ስለመሰጠቱም ተገልጿል።

የጂኦ ፖለቲክስ ትንተና ላይ እንደተመለከተው በምእራባውያን ዘንድ ስለወደፊቱ የኢትዮጵያ እጣ ፈንታን አስመልክቶ ከተደረጉ ውይይቶች መካከል አንዱ አማጺው ቡድን ስልጣን መያዝ የሚችል ከሆነ እና የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም ዝግጁ የሚሆን ከሆነ ክልሎች መገንጠል እንዲችሉ ህዝበ ውሳኔ እንዲያደርጉ ሊፈቅድ እንደሚችል በዝርዝር ውይይት ስለመደረጉ ተጠቅሷል።

ይህ ሁኔታ ለአሜሪካና ለአውሮፓ ህብረት በአንድ በኩል ኢትዮጵያ እንደ ዩጎዝላቪያ የተበታተነች ሀገር እንድትሆን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላቸው፤ በሌላ በኩል የመጨረሻው የዩጎዝላቪያ ፕሬዝዳንት ስሎቦዳን ሚሎሶቪች ላይ እንዳደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይን በሰብአዊ መብት ጥሰት ስም ለዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ለማቅረብ ያለመ መሆኑን ጽሑፉ ያብራራል።   

ጽሑፉ እንደሚገልጸው ኢትዮጵያ አስተዳደሯን ለማላላት ፈቃደኛ ከሆነች ህወሓትን ጨምሮ ሁሉንም ያካተተ ብሔራዊ ውይይት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንኳ በማይሳተፉበት ሁኔታ ሊካሄድ እንደሚችል በምእራባውያን ዘንድ መታሰቡን ያስረዳል። ብሔራዊ ውይይት በሚካሄድበት ወቅት በኢትዮጵያ ያልተማከለ አስተዳደር የሚያጠናክር የህገ መንግስት ክለሳ አስፈላጊነትን ባካተተ መልኩ እንዲሆን እቅድ መያዙም ተገልጿል።           

አሜሪካና የአውሮፓ ህብረት  በኢትዮጵያ ላይ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሴራ እያሴሩ ቀውሱን ለመፍታት እንዴት ይችላሉ? በማለት የሚጠይቀው የጂኦ ፖለቲክስ ትንታኔ ምእራባውያን በሌሎች ሀገሮች መንግስታት ጣልቃ መግባት ሲፈልጉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ እንደሚሰሩ ይጠቁማል። በኢትዮጵያ ላይ በተቀረጸው የትእዛዝ መስጫና መቆጣጠሪያ ማእከል “Command and Control Fusion Center (C2FC)” ፕሮጀክት ራሱን የቻለ ነፃነት ያለው አካል ሲሆን ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል የማማከር፣ የማመቻቸት፣ የመረጃ ስርጭት እና የኢንተሌጀንስ ስራ የሚሉት እንደሚገኙበት አመልክቷል።

የመረጃ ስርጭት (Information capacitance) ለየትኛውም የፕሮፖጋንዳ ስራ ቁልፍ መሆኑን የሚያትተው ጽሑፉ በኢትዮጵያ በተፈጠረው ቀውስ የመገናኛ ብዙሃን በትግራይ ስላለው ጦርነት እና በኦሮሚያ ክልል ስላሉ ታጣቂዎች በሚዘግቡበት ወቅት መንግስትን በሚያጣጥሉና የትግራይና የኦሮሚያ ታጣቂዎችን በሚጠቅሙ መንገድ ዜናዎችን እያዘጋጁ  በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት እንዲሰራጩ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡

የተለያዩ ስብጥሮችን የያዘው ቡድን (Fusion Cells) የታዋቂ መገናኛ ብዙሃን አካላትን፣ ጋዜጠኞችን፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንን፣ የህግ ሰዎችን፣ የዴሞክራሲ ተሟጋቾችን፣ የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞችን፣ የግል ኢንተሊጀንስ ድርጅቶችን፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን እና ምእራብ ዘመም የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች ጋር ቁርኝት ያላቸው ተመራማሪዎችና የምርምር ተቋማትን እንደሚያካትት ትንተናው ያመለክታል። በኢትዮጰያ ላይ ዘመቻ ከከፈቱ የዴሞክራሲ ተሟጋቾች መካከል ተቀማጭነታቸው በኬንያ፣ በታንዛኒያ፣ በኢትዮጰያ፣ በሶማሌያ፣ በኡጋንዳ፣ በአውሮፓ፣ በአሜሪካ እና ኦሺኒያ ያደረጉ መሆናቸውን ጂኦ ፖለቲክስ አመልክቷል።

የቡድኑ የኢንተልጀንስ ተግባር የሚያከናውኑ አክቲቪስቶችንና ገዳይ ጋዜጠኞችን (Lethal Journalism) ያካተተ መሆኑን ያስረዳው ዘገባው የግብረ ሀይሉ አባላት ማናቸውንም ኢትዮጵያን የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚሰስቡ አስታውቋል፡፡ እነዚህን መረጃዎች ከማህበራዊ ሚዲያ፣ ከህወሀት ካድሬዎች፣ ከጦርነቱ ተጎጂዎችና ከትግራይ ዲያስፖራዎች እንደሚያገኙም አመልክቷል፡፡

በዚህ ቡድን ውስጥ ያሉ አባላት የተለያዩ ትርክቶችን በመፍጠርና መልሰው በማስተጋባት እንዲሁም የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ተአማኒነትን የሚያሳጡ መረጃዎች በማፈላለግ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ጽሑፉ ያስረዳል። በቡድኑ አባላት የተፈጠሩ ትርክቶች ወደ መገናኛ ብዙሃን ከመውጣታቸው በፊት ተጽእኖ ፈጣሪ እንዲሆኑ ለማድረግ ወደ ትእዛዝ መስጫና መቆጣጠሪያ ማእከል “Command and Control Fusion Center (C2FC)” እንደሚደርሱ ያመለከተው ጽሑፉ፤ ሬውተርስን የመሳሰሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰፊ ተደራሽነት ባላቸውና በመረጃ የጦርነት ዘመቻ የመክፈት አቅም ባላቸው መገናኛ ብዙሃን እንዲሰራጩ እንደሚደረግ በትንታኔው ተብራርቷል።

መገናኛ ብዙሃኑ የህወሓት አመራሮች እና ሰራዊቱ መልካም ስነምግባር እንዳላቸውና ፕሮፌሽናል እንደሆኑ አድርገው እያሰራጩ መሆኑን አብራርቷል።  የህወሓት የጦር መሪ ጄኔራል ፃድቃን  ገ/ትንሳይ በኬንያ ከሚገኘው ዘ ኤሌፋንት ከተሰኘው መገናኛ ብዙሃን ጋር  በሐምሌ ወር  ላይ ቃለምልልስ ማድረጉን የጠቆመው ጽሑፉ የትግራይ መከላከያ ሃይል የትግራይ ክልላዊ መንግስት ሰራዊት እንጂ የህወሓት ጦር አለመሆኑን በመግለጽ የትግራይ ሰራዊትን ገጽታ ለመገንባት እንደተጠቀሙበት አመልክቷል።

የምእራባውያን መገናኛ ብዙሃን የታለመውን ዓላማ ለማሳካት ገና ከጅምሩ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የህወሓትን ጦር ማሸነፍ እንደማይችል የሚተርኩ ዘገባዎችን ከማሰራጨታቸውም በላይ ሠራዊቱ ጨካኝ መሆኑንና የትግራይን ህዝብ ለመጨረስ ጦርነት መክፈቱን ህወሓት ይህን ለመከላከል መገደዱን በሚያሳይ መልኩ በመዘገብ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ህወሓትን እንዲደግፉ በተቀናጀና በተናበበ መልኩ መልእክት ሲያስተላልፉ መቆየታቸውን ዘገባው አመልክቷል።

የጂኦ ፖለቲክስ ትንታኔ እንደሚያመለክተው ምእራባውያን ህወሓትን በማንገስና ገጽታውን በመገንባት መልሰው ወደ ስልጣን ለማምጣትና የኢትዮጰያን መንግስት ለማዳካም አሊያም የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅመው የመንግስት ለውጥ ለማድረግ በሁሉም አቅጣጫ ዘመቻ ከፍተዋል። ኢትዮጵያውያን በአንፃሩ በሀገር ሉአላዊነት ላይ እንደማይደራደሩ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተደጋጋሚ አሳይተዋል።

በሀገር አቀፍ ምርጫ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ መሪውን የመረጠበት መንገድ አንዱ ማሳያ ነው። ከሰሞኑም የህወሓትን ትንኮሳ በመቃወም ህዝቡ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመሰልፍ የሀገሪቱን አንድነት እንደሚያጠናክር ያስተላለፈው መልእክት ሌላኛው ማሳያ ነው።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም