የጎንደር ጥንታዊ ቤተ መንግስታት ቅርሶች ከጉዳት ለመጠበቅ የጥገና ስራ ተካሄደ

100
ጎንደር ነሓሴ 3/2010 በሀገሪቱ ከመስህብ ሃብቶች አንዱ የሆነውን የጎንደር ቤተ መንግስታት ቅርሶች ከጉዳት ለመጠበቅ ሶስት ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ የጥገና ስራ ተካሄደ፡፡ የጎንደር ከተማ አስተዳደር  ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ለኢዜአ እንደገለጸው የቅርሶቹ ጥገናው የተካሄደው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ውስጥ ነው። በዚህም የአጼ ፋሲል፣ እቴጌ ምንትዋብ፣ አጼ ዳዊትና የአጼ እያሱ ቤተ መንግስታት ከመሰረታዊ ይዘታቸው ጋር የተያያዘ ጥገና እንደተደረገላቸው በመምሪያው የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ አቶ አይቸው አዲሱ ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም የአጼ ፋሲለደስ መዋኛ ገንዳ ወለሉ ላይ የተከሰተውን የውሃ ስርገት ለመከላከል የሚያስችል ጥገናም ተደርጓል፡፡ ቡድን መሪው እንዳሉት  በቅርሶቹ ላይ የደረሰውን የወለልና የግድግዳ መሰነጣጠቅ፣ የጣሪያ ፍሳሽ፣ የበርና መስኮቶች ጉዳት ለመከላከል የሚያስችል ጥገና በዘርፉ ሙያ በተካኑ የቅርስ ጥገና መሃንዲሶች ተካሄዷል፡፡ ጎብኚዎች በቀላሉ ቅርሶቹን ተዘዋውረው መጎብኘት እንዲችሉም ወደ ቤተ መንግስታቱ ግብረ ህንጻዎች የሚያደርሱ የውስጥ ለውስጥ የእግረኛ መንገድ ተሰርቷል፡፡ በተጨማሪም በእርጅና ምክንያት የተጎዱ የአጼ ፋሲል ቤተ-መንግስት መወጣጫ ሰገነቶችም በተካሄደው ጥገና ለአገልግሎት ምቹ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ በጥገና ስራው 98 ለሚሆኑ የጉልበት ሰራተኞች ጊዚያዊ የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ በቤተ መንግስታቱ ግብረ ህንጻዎች የተከናወኑት የቅርስ ጥገና ስራዎች በቅርሶቹ ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ የመከላከል እንጂ ችግሮቹን በዘለቄታ የሚፈታ እንዳልሆኑም ቡድን መሪው ተናግረዋል፡፡ ቅርሶቹን በዘላቂነት ከመጠበቅና ከመንከባከብ አኳያ የሚስተዋለውን የፋይናንስ ችግር ለመፍታት እንዲቻልም በየዓመቱ ከዘርፉ የሚኘው ገቢ ለቅርስ ጥገና ስራ የሚውልበት መንገድ እንዲመቻች ለበላይ አካል ጥያቄ  መቅረቡንም ጠቁመዋል፡፡ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የጎንደር ቤተ መንግስታት ቅርሶች ከ25 ሺህ በላይ በሚበልጡ የውጪ ቱሪስቶች ተጎብኝተዋል፡፡ በከተማው የሚገኙ ሆቴሎች፣ ምግብ ቤቶች፣ የስጦታ እቃ መሸጫዎች፣ መዝናኛ ስፍራዎችና አስጎበኚዎች ከቱሪዝም ገቢው ከ270 ሚሊዮን ብር በላይ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም