በማእከላዊ ጎንደር ዞን 15 ሺህ ሄክታር መሬት በቅመማ ቅመም እየለማ ነው

66
ጎንደር ነሃሴ 3/2010 በማእከላዊ ጎንደር ዞን ስድስት ወረዳዎች  ከ15 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቅመማ ቅመም እየለማ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡ የጎንደር ግብርና ምርምር ማእከል በሽታንና ተባይን ተቋቁሞ ከፍተኛ ምርት መስጠት የሚችል የነጭ አዝሙድ ዝርያ በምርምር በማፍለቅ በአርሶ አደሮች የዘር ብዜት ስራ እያከናወነ መሆኑን አመልክቷል፡፡ የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ጀመረ ለኢዜአ እንደተናገሩት በዘንድሮ የክረምት ወቅት ከ15ሺ ሄክታር በላይ መሬት በቅመማ ቅመም እየለማ ይገኛል። በቅመማ ቅመም እየለማ ካለው መሬት ውስጥ 12ሺ ሄክታሩ በበርበሬ፣ አብሽና ነጭ ሽንኩርት የተሸፈነ ሲሆን ቀሪው ደግሞ በነጭና ጥቁር አዝሙድ እየተሸፈነ ነው ብለዋል፡፡ ነጭና ጥቁር አዝሙድን ከሀገር ውስጥ ገበያ ባለፈ ለውጪ ገበያ መላክ እንዲቻልም በምእራብ ደንቢያና ጣቁሳ ወረዳዎች በኩታ ገጠም እየለማ መሆኑን ተናግረዋል። በወረዳዎቹ በቅመማ ቅመም በመልማት ላይ ካለው መሬት ከ350 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ የጎንደር ግብርና ምርምር ማእከል ኃላፊ አቶ ጸዳሉ ጀንበር በምርምር ያፈለቃቸውንና በብሄራዊ የዘር አጽዳቂ ኮሚቴ እውቅና የተሰጣቸውን ሁለት የነጭ አዝሙድ ዝርያዎች ወደ ዘር ብዜት ስራ እንዲገቡ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ ''ዝርያዎቹ በሽታና ተባይን በመቋቋም ከፍተኛ ምርት መስጠት የሚችሉ ሲሆኑ በጣቁሳ ወረዳ በተመረጡ አርሶአደሮች ማሳ ላይ የዘር ብዜት ስራ እየተከናወነ ይገኛል'' ብለዋል፡፡ በቀጣዩ አመት የተሻሻለውን የነጭ አዝሙድ ዝርያ ወደ አርሶአደሩ በስፋት በማሰራጨት በተባይ ምክንያት የተቸገሩ ቅመም አምራች አርሶአደሮች ወደ ልማቱ የሚገቡበት ሁኔታ እንደሚመቻች ተናግረዋል፡፡ ግብርና ምርምር ማእከሉ ዘመናዊ የቅመማ ቅመም ልማት ቴክኖሎጂዎችንና አሰራሮችን እንዲሁም ለአካባቢው ስነ ምህዳር ተስማሚ ዝርያዎችን እያቀረበልን ነው ያሉት ደግሞ በጣቁሳ ወረዳ ቅመም አምራች የሆኑት አርሶአደር አየልኝ አለሙ ናቸው፡፡ ''በዘንድሮ የክረምት የቅመማ ቅመም ልማት ስራ ማእከሉ ያቀረበልኝን የነጭ አዝሙድ ዝርያ በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ እያባዛሁ ነው' ያሉት አቶ አየልኝ 'እስከ 20 ኩንታል ምርት እንደማገኝ ገምቻለሁ'' ብለዋል፡፡ በቅመማ ቅመም ልማት የተሰማራው ሌላው የዚሁ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ዘላለም አየልኝ ነጭና ጥቁር አዝሙድ በዋጋም ሆነ በተፈላጊነቱ በገበያ እየጨመረ በመምጣቱ በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ነጭ አዝሙድ እያለማ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ''ገበያ ተኮር ሰብሎች የአርሶአደሩን ኑሮና ገቢ የሚያሳድጉ በመሆኑ እኔም በቅመማ ቅመም ልማቱ በመሰማራት ህይወቴን ለመቀየር ጠንክሬ እየሰራሁ ነው'' ብሏል ወጣት ዘላለም ፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም