በምእራብ ሐረርጌ ዞን ዘንድሮ የሚሰጡ አገራዊና ክልላዊ ፈተናዎች ከኩረጃ ነፃ እንዲሆኑ ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለፀ

3727

ጭሮ ግንቦት 8/2010 በምእራብ ሐረርጌ ዞን ዘንድሮ የሚካሄዱት አገራዊና ክልላዊ ፈተናዎችን ከኩረጃ ነፃ ሆኖ በሰላም እንዲጠናቀቁ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁ ተገለፀ፡፡

በዞኑ ከሚገኙ ዘጠኝ መስሪያ ቤቶች የተዋቀረው ግብረሃይል አባላት የትምህርት ጥራት የማስጠበቅ ኃላፊነት የሁሉም ወገን ጉዳይ በመሆኑ  ኃላፊነታቸውን በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት የግብረሃይሉ አባላት መካከል አቶ ብዙነህ ደምሴ እንደተናገሩት ተማሪ ዓመቱን ሙሉ የለፋበት ውጤት በጥቃቅን ችግሮች እንዳይበላሽና ተረጋግቶ ፈተናውን እንዲወስድ ለማድረግ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ይሰራሉ።

”ኩረጃ ከሞራልና ከስነምግባር አንፃር ማህበራዊ ጠንቅ ነው” ያሉት አስተያየት ሰጪው  ከወዲሁ በመከላከል  በራሳቸው የሚተማመኑ የነገ አገር ተረካቢ ዜጎች ለማፍራት ግብረሃይሉ በቅንጅት እየተንቀሳቀሰ  መሆኑን ተናግረዋል ።

በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ የወንጀል መከላከል ክፍል ኃላፊ ኮማንደር ነጋሽ ጢጣ በበኩላቸው የፈተና ሂደቱ ያለ ምንም ችግር እንዲካሄድ በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በሁሉም ወረዳዎች በተዘጋጁ የፈተና ጣቢያዎች  አስፈላጊው የፀጥታ ሃይል በመመደብ ፈተናው በሰላምና ከኩረጃ ነፃ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ የሚረዳ እቅድ ወጥቶ ዝግጅት መጠናቀቁን አስረድተዋል ።

የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሸምሸዲን ኢብራሂም እንዳሉት በዘንድሮ ዓመት በዞኑ ከ30 ሺህ በላይ የ8ኛ፣10ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች በ430 ትምህርት ቤቶች ፈተናውን ይወስዳሉ ።

ግብረሃይሉ አስቀድሞ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረጉ ፈተናው በሰላምና ከኩረጃ ነፃ ሆኖ ይጠናቀቃል የሚል እምነት እንዳላቸው ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል፡፡