ለህልውና ዘመቻው ስኬት የተጀመረው ድጋፍ ተጠናከሮ ይቀጥላል

ጋምቤላ ፤ ሐምሌ 24/2013 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት የከፈተውን ጦርነት ለመቀልበስ በግንባር ለተሰለፉ የሀገር መከላከያና ሌሎች የጸጥታ አካላት የጀመሩትን ድጋፍ እንደሚያጠናክሩ የጋምቤላ ክልል የመንግስት ሠራተኞችና አመራሮች አስታወቁ።

በክልሉ በየደረጃው ያሉ የመንግስት ሠራተኞችና የአመራር አካላት ለህልውና ዘመቻው ከወር ደመወዛቸው ከ10 እስከ 25 በመቶ ለግሰዋል።

ድጋፍ ካደረጉት አቶ ዩኤል ተክሌ ፤የጁንታውን እኩይ ተልኮ ለመቀልበስ በግንባር ለሚገኙ ጀግኞች ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ደማቸውንም እንሰጣለን ብለዋል።

በቀጣይም የህልውናው ዘመቻ በስኬት እስኪጠናቀቅ ድረስ የጀመሩትን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክረው እንሚቀጥሉ ነው ያስታወቁት።

የሽብር ቡድኑ ሀገር ለማፈረስ የከፈተውን ጦርነት ለመቀልበስ በግንባር ላሉ የሀገር መካላከያና የልዩ ኃይል አባላት ድጋፍ እንዲወል ከወር ደመወዛቸው 10 በመቶ መለገሳቸውን የተነጋሩት ደግሞ  አቶ አዲሱ መታፊያ ናቸው።

በቀጣይም  ስከ ህይወት መስዋዕትነት ድረስ ለመክፈል መነሳሳታቸውን አስታውቀዋል።

የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ አቡላ ኡቦንግ በበኩላቸው "በህልውና ዘመቻ በግንባር ለሚገኘው ሠራዊት በደም ልገሳ፣ በገንዘብና በሌሎች የተጀመረው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።

ከደም ልገሳ በተጨማሪ ከወር ደመወዛቸው 25 በመቶ መለገሳቸውን ተናግረዋል።

በጥፋት ተግባር የተሰማራው የህወሓት ርዝራዥ ቡድን የከፈተውን ጦርነት ለመቀልበስ እየተካሄደ ያለውን እንቅስቀሴ ለመደገፍ እየተሰራ መሆኑን ያስረዱት ደግሞ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መሰተዳድርና የድጋፍ አሰባሰቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተንኳይ ጆክ ናቸው።

"በዚህም በግንባር ለተሰለፈው የመከላከያ ሠራዊት ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ በዓይነትና ጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ለመሰብሰበ ታቅዶ ወደተግባር ተገብቷል" ብለዋል።

በእስካሁኑ ሂደት ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ የመንግስት ሠራተኞችና የአመራር አካላት ከወር ደመወዛቸው ላይ ከ10 እስከ 25 በመቶ መለገሳቸውንም ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በክልሉ የሚገኙ 56 የመንግስት ተቋማት ለሥራ ማስኬጃ ከተመደበላቸው ገንዘብ ላይ ከ100 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር ለመገለስ ቃል መግባታቸውን ነው አቶ ተንኳይ ያስታወቁት።

 የንግዱ ማህበረሰብና ሌሎች  የህብረተሰብ ክፍሎች ከ40 በላይ ሰንጋዎችና ከ1 ሚሊዮን 300 ሺህ ብር በላይ በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።

የተሰባሰበውን ድጋፍ በቅርቡ ግንባር ድርስ በመሄድ ለሠራዊቱ አባላት እንዲደርስ የሚደረግ መሆኑንም አቶ ተንኳይ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም