አፍሪካ ወደ መካከለኛ ገቢ ደረጃ ለመሸጋገር ሙስናን መዋጋት የትኩረት አቅጣጫዋ አድርጋ መሥራት አለባት

105
አዲስ አበባ ነሀሴ 2/2010 አፍሪካ ወደ መካከለኛ ገቢ ደረጃ ለመሸጋገርና የበለጸገች አህጉር ለመሆን ሙስናን መዋጋት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዋ አድርጋ መሥራት እንዳለበት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ቬራ ሶንግዌ ገለጹ። በርዋንዳ ርዕሰ መዲና ኪጋሊ ለሁለት ቀናት በተካሄደው የአፍሪካ የአመራሮች ስብሰባ ላይ ዋና ፀሐፊዋ እንደገለጹት፤ የአፍሪካ መሪዎች ሙስናን፣ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን እና የታክስ ማጭበርበርን ለመከላከል ትኩረት ሰጥተው መስራት አለባቸው። አፍሪካ የልማት ግቦቿን ለማሳካት ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስፈልጋት ሲሆን የፍትህ ተቋማት፣ ዋና ኦዲተሮች፣ ዳኞችና የመገናኛ ብዙኃን ሙስናን ለመከላከል የሚደረገውን የጋራ ጥረት መደረገፍ አለባቸው ብለዋል። መሪዎችና ባለስልጣናት እንዲሁም በፋይናንስ ዘርፍ የተሰማሩ የግል ተቋማት ኃላፊዎች ተጠያቂነትና ግልጽነት ያለው አሰራር ሊከተሉ እንደሚገባ ገልጸዋል። የአፍሪካ አገራት የታክስ መረጃዎችን መለዋወጥ የሚያስችል ዓለም አቀፍ የታክስ መረጃ ስምምነቶችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። በተጨማሪም አገራት ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር መከላከል ላይ የሚሰሩ ተቋማትን በሰለጠነ የሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራርን ማብቃት እንዲሁም የሚኒስትር መስሪያ ቤቶችና ሌሎች የመንግስት ተቋማት ተገቢ የሚባሉ መረጃዎችን መለዋወጥ የሚያስችላቸውን ስርአት መዘርጋት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል የተዘጋጁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ፈርሞና በአገራቸው ፓርላማ አጸድቀው ወደ ስራ ያስገቡ የአፍሪካ አገራትን አድንቀዋል። መንግስታት ሙስናና ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል በተለያዩ አቅጣጫዎች እርምጃ ለመውሰድ የአመራርነት ብቃትን ማሳደግ ወሳኝ ሚና እንዳለው አመልክተዋል። አፍሪካ ባለፉት ሦስት አስር አመታት በሙስና እና በህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወደ 1 ነጥብ 4 ትሪሊዮን የሚጠጋ ዶላር አጥታለች። እ አ አ ከ2005 እስከ 2014 ድረስ ባሉት ዓመታት ከንግድ ሥርዓት ውጪ በዓመት በአማካይ 27 ቢሊዮን ዶላር ማጣቷን መረጃዎች ይጠቁማሉ። የአፍሪካ መሪዎች የመገማገሚያ መድረክ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ ለመድረኩ ባቀረቡት ሪፖርት በህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር አፍሪካ በየዓመቱ ከ50 እስከ 80 ቢሊዮን ዶላር ታጣለች። በርዋንዳ ርዕሰ መዲና ኪጋሊ ለሁለት ቀናት በተካሄደው የአፍሪካ የአመራሮች ስብሰባ ላይ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ፣ የቀድሞው የታንዛንያ ፕሬዚዳንት ቤንጃሚን ምካፓ፣ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ፣ የቱኒዚያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት መሐመድ ሞኔፍ እና የቀድሞ የሞዛምቢክ አርማንዶ ጉቡዛ መሳተፋቸውን የአፍሪካ ኀብረት ለኢዜአ የላከው መግለጫ ያመለክታል። የአፍሪካ ኀብረት ጥር 21 እና 22 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ባካሄደው 30ኛው የመሪዎች ጉባዔ የፈረንጆቹ 2018 ዓመት የአፍሪካ የፀረ ሙስና ዓመት ብሎ መሰየሙ የሚታወስ ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም