አሸባሪው ህወሃት የትግራይ እናቶችን በማስገደድ ልጆቻቸውን ለጦርነት አሰልፎ አረመኒያዊ ተግባር እየፈጸመ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 23/2013(ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት የትግራይ እናቶችን በማስገደድ ልጆቻቸውን ለጦርነት አሰልፎ አረመኒያዊ ተግባር እየፈጸመ መሆኑን የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) አመራር አባላት አስታወቁ።

አሸባሪው ህወሃት ሥልጣኑን ለማራዘም "የትግራይን ህጻናት መገበር ልማዱ ነው" በማለት ገልጸውታል።

 የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራር ከትግራይ ክልል ውጪ ያሉ የክልሉ ተወላጆች ከመላ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን በአሸባሪ ቡድኑ ለታፈኑ ወገኖቹ ድምጽ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተሻለ ንጉሴና የፓርቲው የፖለቲካ ጉዳይ ሃላፊ አቶ ሀጎስ ግደይ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ሃላፊዎቹ እንደተናገሩት፤ አሸባሪ ቡድኑ ለፖለቲካ ትርፍ ሲል በትግራይ ታዳጊዎች ላይ ከፍተኛ ግፍና በደል ሲፈጽምና የህጻናትን መብት ሲጥስ ቆይቷል።

የትግራይ እናቶች ወደው ሳይሆን ተገደው ልጆቻቸው በየጊዜው ለጦርነት እንዲማገዱ መደረጋቸውን ያስታወሱት ሃላፊዎቹ፤ የዚህ ዓይነቱ ድርጊት ቡድኑን በዓለምአቀፍ ህግ እንዳያስጠይቀው በማሰብ መረጃ ሲደብቅ መኖሩን ተናግረዋል።

የፓርቲው ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተሻለ ንጉሴ እንደሚሉት፤ አሸባሪው ህወሃት በትግራይ ህዝብ ላይ የፈጸማቸው ግፎችና በደሎች ይፋ እንዳይወጡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርግ ነበር።

ከዚህ ውስጥ ድርጅቱ ወደ ስልጣን ሲመጣ ከ60 ሺ በላይ ዜጎች መስዋዕት መሆናቸውን መግለጹን አስታውሰው፤ በወቅቱ ተገደው የተሳተፉ አቅማቸው ለጦርነት ያለደረሰ ወጣቶች መረጃ ግን እንዲጠፉ ማድረጉን አብራርተዋል።

የፓርቲው የፖለቲካ ጉዳይ ሃላፊ አቶ ሀጎስ ግደይ በበኩላቸው፤ ለትግራይ ህዝብ ጠላቱ አሸባሪ ቡድኑ ነው።  ይህ አሸባሪ ቡድን ለሥልጣን መራዘም ሲል ወጣቱን መገበር ልማድ አድርጎ እስከአሁን መዝለቁን ገልጸዋል።

የትግራይ ህዝብ "አሸባሪው ህወሃት ተመልሶ ሥልጣን ይይዛል" የሚል ከንቱ ተስፋ መያዝ እንደሌለበት  ያሳሰቡት የፓርቲው የስራ ሃላፊዎች፤ ህዝቡ ራሱ በፈጠረው ስዕል ካልሆነ በቀር የሽብር ቡድኑ መዋቅር መበጣጠሱን አብራርተዋል። 

አሸባሪው ህወሃት የዘረጋው ስርዓት መፍረሱንና የሽብር ቡድኑ ከጥቂት ሽፍቶች በስተቀር መክሰሙንም አመልክተዋል። 

በውጭ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች የአሸባሪውን ቡድን ውለታ ለመክፈል ሲሉ በህዝባቸው ላይ የሚደርሰውን ግፍና በደል ለመደበቅ እየሞከሩ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የትግራይ ህዝብ ህልውና የሚከበረው በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ መሆኑን አጽንኦት የሰጡት ሃላፊዎቹ፤ እነርሱ በተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ደሃውን ህዝብ ለጦርነት እንዲማገድ ማድረጋቸው ከራሳቸው ውጪ ለሌላው አለማሰባቸውን እንደሚያሳይ አብራርተዋል።

ከትምህርት ከቀረው የትግራይ ታዳጊና የምግብና የመድሃኒት እጥረት ከሚያሰቃየው ህዝብ ጉዳይ ይልቅ የአሸባሪው ህወሃት ህልውና የሚያሳስባቸው ሆነው እንደተገኙም ነው የተናገሩት።

በዚህ ተግባራቸው የፖለቲካ ቀውሱን በማባባስ ከህግ ቢያመልጡም ከህሊና ተጠያቂነት አያድናቸውም ነው ያሉት።

የትግራይ ህዝብ ያለምንም ምክንያት ለገበረው ልጁ ካሳ የሚሆነው የአሸባሪ ቡድኑ መጥፋት መሆኑንም ገልጸዋል።

የትግራይን ህዝብ ከሽብርተኛው ቡድን ግፍና በደል ነጻ ለማውጣት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ጠቁመው፤ "ይህም ህዝቡ ለወገኑ ያለውን አጋርነት ማሳያ ነው" ብለዋል።

ቡድኑ በተለይም በትግራይ ክልል የሚኖረውን የክልሉ ተወላጅ በተለያዩ መዋቅሮች ጠርንፎ እንዳይንቀሳቀስ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡

ይህን ተከትሎ በሌላው አካባቢ ያሉ የትግራይ ተወላጆች የታፈኑ ወገኖቻቸውን ነጻ ለማውጣት ድምጻቸውን ማሰማት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

መንግስት በትግራይ ክልል የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ከወሰነባቸው ምክንያቶች አንዱ የሰብዓዊ አቅርቦት እንዳይስተጓጎል ቢሆንም፤የሰብዓዊ አቅርቦት እንቅስቃሴው በአሸባሪው ህወሓት ትንኮሳዎች እየተደናቀፈ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም