የኪነ-ጥበቡ ማኅበረሰብ ሀገር የማዳን ዘመቻውን በሙያው ማገዝ አለበት - ኢዜአ አማርኛ
የኪነ-ጥበቡ ማኅበረሰብ ሀገር የማዳን ዘመቻውን በሙያው ማገዝ አለበት

ሐምሌ 23/ 2013 ዓ.ም(ኢዜአ) የኪነ-ጥበቡ ማኅበረሰብ ሀገር የማዳን ዘመቻውን በሙያው ማገዝ እንዳለበት የመከላከያ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ጥሪ አቀረቡ።
የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ለሀገር ህልውና ያላቸው ሚና ላይ ትኩረት ያደረገ የውይይት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ብዙነሽ መሰረትን ጨምሮ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ወታደራዊ መኮንኖች እንዲሁም የተለያዩ የኪነ-ጥበብ ሙያተኞች በተገኙበት ተካሂዷል።
የመከላከያ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮሎኔል ጌትነት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያውያን በየዘመናቱ የገጠሟቸውን የውጭ ወራሪዎችና ውስጥ ፀረ-ሰላም ኃይሎች በድል ሲመክቱ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
ሆኖም የህወሃት አሸባሪ ቡድን ጥቅምት 24ቱ የሰሜን ዕዝ አባላት ላይ የፈጸመው ጭካኔ በቃላት መግለጽ ከባድ መሆኑን አመልክተው "የኢትዮጵያ ሠራዊት ህዝብን ከጠላት ለመከላከል በምሽግ ላይ እንዳለ ከምስረታው ጀምሮ ኢትዮጵያውያንን ወዳጅና ጠላትነት ጎራ ከፍሎ በተመሰረተው ቡድን ከጀርባ ተወግቷል፤ ይህስ በምን ይገለጻል" በማለት ጠይቀዋል።
የመከላከያ ሰራዊቱ የህወሃት አሸባሪ ቡድንን ጨምሮ ሌሎች ጠላቶችን ለመመከት ዝግጁ መሆኑንም አስታውቀው አሁናዊ ሁኔታው የስነ ልቦና ጦርነት እንደመሆኑ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በተናጠልም ሆነ በቡድን ሆነው ሀገር የማዳን ዘመቻውን የሚያግዙ የፈጠራ ስራዎችን እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል።
የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክቶሬት ተወካይ ብርጋዴር ጀኔራል አስፋው ማመጫ በበኩላቸው ኪነ-ጥበብና መከላከያ የአንድ ሣንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው፤ "የመከላከያ ሠራዊቱ ለኪነ-ጥበብ ትልቅ ስራ ሰርቷል፤ ስመ-ጥር የጥበብ ሰዎችንም አፍርቶ ለሀገር አብቅቷል" ብለዋል።
ኢትዮጵያ በየዘመናቱ የገጠሟት ጠላቶች እንዲወድቁና ሀገር ድል እንድትነሳ ኪነ-ጥበብ ትልቅ ሚና እንደነበረው አውስተው ጀግንነት፣ አርበኝነት፣ የሀገር ፍቅርና አሸናፊነት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ባሕል እንዲሆን ኪነ- ጥበብ በጎ ሚና ማበርከቱንም ብርጋዴር ጀኔራል አስፋው ተናግረዋል።
በሶማሊያ ወረራ ወቅት የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የነበራቸውን ጉልህ ሚና ለአብነት ጠቅሰው በቀጣይም ሀገር ለማዳን በሚደረገው ትግል በመሳተፍ ደማቅ ታሪክ እንዲጽፉ አደራ ብለዋል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒትር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት፤ መድረኩ የኪነ-ጥበብ ማህበረሰቡ ለሠራዊቱ ያለውን ድጋፍ ለማሳየት መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ኪነ ጥብብ በደስታ ብቻ ሳይሆን በችግር ጊዜም እስከ ጦር ሜዳ ድረስ በመሄድ ጠላትን ደል ለመንሳት ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
በዚህም የኪነ-ጥበቡ ማህበረሰብ ኮሚቴ አዋቅሮና የአጭር፣በመካከለኛና ረዥም ጊዜ እቅድ ይዞ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።