የድሬዳዋን ሰላምና ፀጥታ ለማስከበር የከተማዋ ወጣቶች በተደራጀ መንገድ እየሰሩ ነው

72
ድሬደዋ ነሀሴ 2/2010 የድሬዳዋ ሰላምና ፀጥታን በማስከበር የተጀመረውን የለውጥ ጉዞና የልማት ተግባራት ለማጠናከር ወጣቶች ተደራጅተው እየሰሩ መሆናቸውን ተናገሩ። ባለፈው እሁድ የተፈፀመው ኢሰብአዊ ድርጊትንም ወጣቶቹ አውግዘዋል፡፡ በድሬዳዋ ገንደገራዳ ቀበሌ 09 ሦስት  መንደሮች ሰሞኑን በተፈፀመው ድርጊት የ14 ሰዎች ሕይወት አልፏል፤ ሃብትና ንብረት ወድሟል፡፡ ችግሩ በተከሰተበትና በሌሎች ቀበሌዎች የሚኖሩ ወጣቶች ተደራጀተው ችግሩን እንዳይስፋፋ ለማድረግና የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ከፀጥታ አስከባሪዎች ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ “የቀበሌ 09 ነዋሪ ወጣት በሐብቱ ካሳዬ እንዳለው የአካባቢው ህብረተሰብ ሰላምና ፀጥታ ለመጠበቅ ወሳኝ በመሆኑ በሥራው ላይ በፍቅር ተሳትፈናል” ብሏል፡፡ “በተከሰተው ችግር ሳቢያ የጠፋው ጥፋት የሚያሳዝንና የሚወገዝ ነው፤ መሰል ችግር እንዳያጋጥም  ለዘመናት  በፍቅርና በአንድነት የተገነባውን የድሬዳዋ ማንነት በመጠበቅ ለአገራችን ዕድገት ተባብረን እንሰራለን” ብሏል፡፡ ወጣት ፋሚ አብዱልከሪም በበኩሉ በፈረቃ ተከፋፍለው  የአካባቢያቸውን ሰላም እየጠበቁ መሆናቸውን ገልጾ የመደመርና የለውጥ ጉዞ ያልተዋጠላቸው ፀረ ሰላም ኃይሎች ሰላማቸውን ለማደፍረስ እየፈጸሙት ያለውን ድርጊት እንደሚያወግዝ አስታውቋል፡፡ ‹‹ሰላም ለአገር ዕድገት ወሳኝ ነው፤ ሰላም ከደፈረሰ ህጻናትና አዛውንቶች ይጎዳሉ፤ ሰርቶ መኖር የሚቻው ሰላም ሲኖር ነው፤ ለአካባቢያችንና ለአገር ዕድገት ወሳኝ በመሆኑ ከፀጥታ አካላት ጋር እየሰራን እንገኛለን›› ብሏል፡፡ በለገሀሬ ቀበሌና አካባቢው ሰላምና ፀጥታን አስተማማኝ ለማድረግ ወጣቶች ያለማንም ጎትጓች እየሰራን እንገኛለን፡፡” ያለችው ደግሞ ወጣት ኢማን መሐመድ ናት፡፡ ተሸከርካሪዎችን እና እግረኞችን በመፈተሽ የተከለከሉ የስለት መሳሪያዎችን በመሰብሰብ ለፀጥታ ኃይሎች በማስረከብ ላይ መሆናቸውን ተናግራለች፡፡ ወጣት ዘከሪያ ሐሰን በበኩሉ በየትኛውም ሥፍራ የሚገኙ የድሬዳዋ ወጣቶች በብሔርና በእምነት ሳይከፋፈሉ የፀረ-ሰላም ኃይሎችን ድርጊት መመከት ለድሬዳዋና ለአገራቸው ዕድገት መስራት እንዳለባቸው ተናግሯል፡፡ ችግሩ በተከሰተበት ስፍራ የሚኖሩት ወይዘሮ ፈሪያ መሊዮን በበኩላቸው “ወጣቶች ለአካባቢያቸው ሰላም መጠበቅ እያደረጉት ባለው አስተዋጽኦ ነዋሪው ሰላሙን እያገኘ ነው” ብለዋል፡፡ የሰሞኑ ችግር ለዘመናት በእምነት፣ በባህልና በጋብቻ በተገማመደው በኦሮሞና በሶማሌ ህዝቦች መካከል የተፈጠረ ሣይሆን ዘራፊዎችና ፀረ ሰላም ኃይሎች የፈጠሩት ችግር ነው፤ ቤቴ ከመቃጠልና  ከመዘረፋ  የተረፈው በጎረቤቶች ጥረትና ፍቅር  ነው፤ ይህን አንድነት አጠናክረን እንቀጥላለን›› ብለዋል፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ህዝብ ግንኙነት ዲቪዥን ኃላፊ ዋና ሳጂን ባንተአለም ግርማ በአብዛኛዎቹ የድሬደዋ ቀበሌዎች ወጣቶች ተደራጅተው ከፀጥታ አካላት ጋር ለሰላም መስፈን እያበረከቱት የሚገኙት አስተዋጽኦ በአርአያነት እንደሚጠቀስ ተናግረዋል፡፡ ይህን ተግባር በማጠናከር ለጥፋት  ሀይሎች የማትመች ድሬደዋን ለመፍጠር ጥረታቸውን በሙሉ አቅማቸው እንዲያጠናክሩም ዋና ሳጂን ባንተአለም ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ በዛሬ እለት ሰሞኑን ችግር በተፈጠረባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትና የትራንስፖርት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ተከፍተው እየሰሩ መሆናቸውን የኢዜአ ሪፖርተር በአካባቢው በመዘዋወር አረጋግጧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም