የተበላሹ እና ከባዕድ ነገሮች ጋር የተቀላቀሉ ምግብ ነክ ምርቶች በተገኙባቸው ተቋማት ላይ እርምጃ ተወሰደ

110
አዲስ አበባ ነሀሴ 2/2010 በአዲስ አበባ የተበላሹ እና ከባዕድ ነገሮች ጋር የተቀላቀሉ ምግብ ነክ ምርቶች በተገኙባቸው 2 ሺህ 600 ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱን የአዲስ አበባ ምግብ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር እና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ። 71 ሺህ ኪሎ ግራም የተበላሹ እና ከባዕድ ነገሮች ጋር የተቀላቀሉ ምግብ ነክ ምርቶች፣ 53 ሺህ ሌትር የተበላሹ የመጠጥ ምርቶች መያዛቸውንም ገልጿል። እንዲሁም ከ5 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ 2 ሺህ 631 ኪሎ ግራም የሚመዝን የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶችን ተይዘው መወገዳቸው ተገልጿል። የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አለምፀሀይ ጳውሎስ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት "የጤና አገልግሎት ጥራትና ብቃትን ለማረጋገጥ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር ባደረገው ክትትል ህገ-ወጥ ድርጊት የሚፈጽሙትን ይዟል"። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተደረገው ዳሰሳ አብዛኞቹ የምግብና መጠጥ ተቋማት የንጽህና ሁኔታ ከደረጃ በታች መሆኑን ተናግረዋል። በከተማው ካሉ ከ1 ሺህ 500 የምግብና የመጠጥ ማምረቻ ተቋማት ውስጥ 52 በመቶ የሚሆኑት በተቋማት የደረጃ ፍረጃ ቀይ መስመር ውስጥ መሆናቸውን ወይዘሮ አለምጸሃይ ተናግረዋል። በዚህም መሰረት የተበላሹ እና ከባዕድ ነገሮች ጋር የተቀላቀሉ ምግብ ነክ ምርቶች በተገኙባቸው 52 ተቋማት እስከ ስድስት ወር አገልግሎት መስጫቸው እንዲታሸግ የተደረገ ሲሆን ሁለቱ ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ ለአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ተላልፏል። ባለፉት ዓመታት የጤና ተቋማትን አገልግሎት ለማሳደግ በተሰራው ስራ 98 በመቶ የሚሆኑት የጤና ተቋማት አረንጓዴ መስመር ውስጥ መግባታቸውን ጠቁመዋል። በቀጣይ የምግብና የመጠጥ ማምረቻ ተቋማትን ደረጃ ለማሳደግ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም