ቀጥታ፡

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለሠራዊቱ ድጋፉን አጠናክሮ ቀጥሏል

ባህር ዳር ሐምሌ 22/2013(ኢዜአ) የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ለመከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ቀጥሏል።
ተቋሙ በሀገራዊ ጉዳዮች ለሚቀርቡ ጥሪዎች ተገቢውን ምላሽ እየሰጠ ይገኛል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ በኮቪድ-19ኝ እና ሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ላይ በሰው ሃይል፣ በቁሳቁስ፣ በገንዘብ፣ በዲፕሎማሲና በተለያዩ መንገዶች አስፈላጊው ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።

አሁንም ኢትዮጵያ በገጠማት የህልውና ችግር መንግስት ያቀረበውን ጥሪ በመቀበል የተቋሙ መምህራንና ሠራተኞች የወር ደመወዛቸውን ከ33 ሚሊዮን ብር በላይ ለግሰዋል።

በተጨማሪው የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ከምግባቸው በመቀነስ 1 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሲሆን፤ የግብርና ኮሌጅም 40 የቁም እንስሳት ድጋፍ አድርጓል።

 የዩኒቨርሲቲው የውስጥ ግንኙነትና ተግባቦት ዳይሬክተር ዶክተር ታደሰ አክሎግ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳብራሩት፤በቀጣይም የተቋሙ  ማህበረሰብ መንግስት ለሚያቀርበው ጥሪ ሁሉ የሚጠበቅበትንአስተዋጽኦ ለማድረግ በቁርጠኝነት ተዘጋጅቷል።

በዩኒቨርሲቲው የጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ሕክምና ባለሙያና የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴው አባል ዶክተር ደግአለም ባዬ ፣ በአውደ ውጊያ ጉዳት ለሚደርስባቸው የሠራዊት አባላት ልዩ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ግብረ ሃይል እየተዋቀረ ነው ብለዋል።

በግንባር አሻባሪውን ህወሓት የሚፋለሙ የሀገር ጀግኖች በአገልግሎታቸው ልክ የሚመጥን የህክምና አገልግሎት ለመስጠት የሰው ሃይል፣ የግብዓትና የቁሳቁስ ማሟላት ሥራ መከናወኑን አስታውቀዋል።

የሆስፒታሉ ሐኪሞች መንግስት ጥሪ ካደረገላቸው ግንባር ድረስ በመሄድ በሙያቸው አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ናቸው ብለዋል።

በግንባር የመጀመሪያ የሕክምና እርዳታ የሚሰጡ በጎ ፈቃደኞችን፣ የሠራዊት አባላትንና ወጣቶችን በአጫጭር ስልጠና ለማብቃት ወስነው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ዶክተር ደግዓለም  አመልክተዋል።

ተማሪዎች ከቁርስና ከሥጋ ወጪያቸው በመቀነስ 1 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ ማድረጋቸውን የገለጸው ደግሞ የዩኒቨርሲቲው  የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት ተማሪ አብርሃም ታደሰ ነው።

ተማሪ አብርሃም እንዳለው፤ በተጨማሪም በግንባር ጉዳት ለሚደርስባቸው የመከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ደም በመለገስ በደም እጦት የሰው ህይወት እንዳይጠፋ እየሰሩ ይገኛሉ።

የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በህልውና ዘመቻው ላይ በሚችሉት አቅም ሁሉ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ቁርጠኛ ናቸው።

ከአሸባሪው የህወሓት ቡድን ጋር የሚካሄደው ጦርነት በድል እንዲጠናቀቅም ሆነ ከድል በኋላ በሚጠበቅባቸው ሁሉ ለማድረግ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን የክልሉን መንግስት ጥሪ እየተጠባበቁ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም