ቀጥታ፡

የአባቶቻችንን የጀግንነት ታሪክ ለመድገም ተነስተናል

ሐረር ፤ ሐምሌ 22 ቀን 2013 (ኢዜአ) በመንግስት የተላለፈውን ጥሪ ተቀብለን የአባቶቻችንን የጀግንነት ታሪክ ለመድገም ተነስተናል።
ሱራፌል ዝናቡ  መከላከያ ሠራዊትን በመቀላቀል የህወሓትን የጥፋት ተግባር ለማክሸፍ  ወስኖ  ከሚኖርበት ሐረሪ ክልል ለተመሳሳይ ዓላማ  ለመዝመት ዛሬ ሽኝት ከተደረገላቸው ወጣቶች መካከል አንዱ ነው።

ወጣት ሱራፌል ሠራዊቱን ለመቀላቀል በፍላጎት መነሳቱንና በዚህም ደስተኛ እንደሆነ ነው የተናገረው።

"እናቴ ደስተኛ ሆና መርቃ ነው የሸኘችኝ፤ በዚህም ደስታ ተሰምቶኛል፤ እስከመጨረሻው የሀገሬን ሉዓላዊነት አስከብራለሁ" ብሏል።

“ከዚህ በፊትም መከላከያ ሠራዊትን የመቀላቀል ፍላጎት ነበረኝ፤ አንድ ነፍሱን ለሀገርና ለህዝብ ሲል ከሚሰጥ ሠራዊት ጋር በመቀላቀሌ ደስተኛ ነኝ" ያለው ደግሞ ወጣት አብዱልፈታህ መሀመድ ነው።

ሌሎች ወጣቶችም ሀገራቸውንና አካባቢያቸውን ከጠላት ለመጠበቅ በቁርጠኝነት በመነሳት ሀላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርቧል።

ከአራት ዓመት በፊት የመከላከያ ሠራዊትን ለመቀላቀል ፍላጎት እንደነበረውና ለእናቱ ብቸኛ ልጅ መሆኑን የገለጸው ወጣት ሔኖክ ለማ በበኩሉ፣ ሀገር ለዜጎች ጥሪ ባቀረበችበት በአሁኑ ወቅት ፍላጎቱ በመሳካቱ መደሰቱን ነው የገለጸው።

በዚህም የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ትግል መንግስት በሚሰጠው ግዳጅ ሁሉ ተሰማርቶ በጀግንነት ለመወጣት ተዘጋጅቷል።

ወጣት ብሩክ ጌታቸው በበኩሉ "ሀገርና ህዝብን ለማዳን የተላለፈውን ጥሪ ተቀብዬ መከላከያ ሠራዊቱን በመቀላቀሌ ደስታ ተሰምቶኛል" ብሏል።

የአባቶችን የጀግንነት ታሪክ ለመድገም መነሳቱን የገለጸው ወጣቱ፣ የሀገርን ሉአላዊነት ለማስከበር  በቁርጠኝነት ለመታገል ወስኗል።

በአሸኛኘቱ ሥነሥርዓት የተገኙት የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ፤ ወጣቶቹ የሀገርን ጥሪ ተቀብለው በሠራዊቱ ውስጥ ለመሳተፍ በመወሰናቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ወጣቶቹ ካለማንም ጫና በፍላጎታቸው መከላከያ ሠራዊቱን መቀላቀላቸው በቀጣይ ለሚያከናውኗቸው ተግባራት ውጤታማነት ሚናው የጎላ እንደሆነ ነው የገለጹት።

ወጣቶቹ በክህሎትና በስነልቦና ራሳቸውን ማዘጋጀትና በተለይ በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች ሁሉ የመከላከያ ሠራዊቱን እሴት እንዲያከብሩም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የክልሉ መንግስትም ለወጣቶቹ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ  አረጋግጠዋል።

በሽኝቱ ሥነ-ሥርዓት የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፤ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች  ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም