አሸባሪው ህወሃት ወልዲያን በሃሰት ፕሮፓጋንዳ ለመረበሽ የሚያደርገው ጥረት አይሳካለትም - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሃት ወልዲያን በሃሰት ፕሮፓጋንዳ ለመረበሽ የሚያደርገው ጥረት አይሳካለትም
ወልዲያ፤ሐምሌ 22/2012(ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት ወልዲያን በሃሰት ፕሮፓጋንዳ ለመረበሽ የሚያደርገው ጥረት አይሳካም።
ወጣት አሰፋ ቦጋለ ተወልዶ ባደገባት ወልዲያ ዙሪያ አሸባሪው ህወሃት በሚያሰራጨው የሃሰት መረጃ ህዝቡን በማተራመስ ለዘረፋ ለማመቻቸት የሚያደርገውን ጥረት አጥብቀው ከሚቃወሙት የከተማዋ ወጣቶች አንዱ ነው።
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርቱን በመጀመሪያ ዲግሪ በማጥናት አራተኛ ዓመት የደረሰው ይህ ወጣት ለእረፍት ወደ ቤተሰቦቹ በሔደበት ህወሃት በሃሰተኛ መረጃ የከተማውን ህዝብ በመረበሽ ለዝርፊያ ለማመቻቸት የሚያደርገውን ጥረት ከጓደኞቹ ጋር ለመከላከል እየሰራ ይገኛል።
በሽብር ድርጊቱ የሚታወቀው የህወሃት ጁንታ ቡድንን ለመከላከል በሚደረገው ጥረትም ከሌሎች የከተማው ወጣቶች ጋር በመሆን ከሚያከናውነው የማረጋጋት ስራ ባለፈ ተገቢውን ዋጋ ለመስጠት ወታደራዊ ስልጠና በመውስድ አስፈላጊውን የመከላከል ስራ ላይ መሳተፍ እንደሚፈልግ ይናገራል።
ትምህርትም ሆነ ማንኛውም ስኬት ሊኖር የሚችለው የተረጋጋ ሃገር ሲኖር እንደሆነ የተናገረው ወጣቱ፤ ጁንታው እስኪደመሰስና ዘላቂ ሰላምም እስከሚረጋገጥ ድረስ ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ተዘጋጅቷል።
አገር አደጋ ላይ ስትወደቅ ዝም ብሎ መመልከት ስለሌለበትም ለጊዜውም ቢሆን አጭር ወታደራዊ ስልጠና ወስዶ መከላከያ ስራዊትን ለማገዝ ተመዝግቧል።
"እኔ ነጋዴ ነኝ፣ እኔ መምህር ነኝ፣ እኔ ሃኪም ነኝ" እና ሌሎችንም ማለት የሚቻለው በህጻናት መስዋዕትነት ሃገር የማፍረስ ምኞቱን ለማሳካት የሞት ሞቱን እየተወራጨ የሚገኘውን አሸባሪውን የህወሃት ቡድን ቅዠት ለማምከን ማንኛውን ተልዕኮ ለመወጣት ተዘጋጅቷል።
ይህንን ስሜት ወጣት መምህር አማኑኤል አማረ ይጋራዋል።
በወልዲያ ከተማ በሚገኘው ጣይቱ ብጡል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር የሆነው ይሄ ወጣት መንግስት ያወጀውን የክተት ጥሪ በራሱ ፍላጎት ተቀላቅሎ ኢትዮጵያ አሁን ያጋጠማት ችግር እስኪወገድ ድረስ የዜግነት ግዴታዬን እወጣለሁ ይላል።
የአገር ህልውና አደጋ ላይ ሲወድቅ ሁሉም ዜጋ ሃላፊነት እንዳለበት የገለጸው መምህር አማኑኤል ከወገን ሰራዊት ጎን ከመሰለፍ ባለፈ በሃሰተኛ ፕሮፓጋንዳ ሃገር ማፍረስ እንደማይቻል አካባቢውን በመጠበቅ በተግባር እያሳየ ይገኛል።
የወልዲያ ባጃጅ ታክሲ አሽከርካሪው ወጣት ሳሚ ዓለሙ በበኩሉ የተለመደና ድሮም የሚታወቅበትን የሃሰት መረጃ በማሰራጨት ሽብር ለመፍጠር የሚሞክረውን የህወሃት ጁንታ ፍላጎት ለማክሸፍ ከከተማው ነዋሪ ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው።
የቆሸሸ ስብዕና ይዘው በጀግኖች ልጆቿ የተከበረች ታሪካዊት ሃገርን ለማፍረስ በአሸባሪው ቡድን የሚደረገውን ጥረት ሙሉ ለሙሉ ለማስወገድ በሚደረገው ትግል ውስጥም ግንባር ቀደም ሆኜ እሰለፋለሁ ይላል።
ለዚህ እንዲረዳውም አስፈላጊውን ስልጠና ለመውሰድና ከሰራዊቱ ጋር ለመሰለፍ በቂ ዝግጅት ያደረገ ሲሆን እስከዛ ድረስ ግን ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር በመሆን ከተማዋን እየተዘዋወረ በሃሰት ወሬ ሰላሟን ለማወክ የሚሞክሩ አካላትን መከታተል ስራው ሆኗል።
አሸባሪው ህወሃት ሃገር የማፍረስ ፍላጎቱን ለማሳካት የሚያደርገውን ሴራና የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ለማክሸፍ መላ ኢትዮጵያዊያን ከዳር እስከዳር በጋራ መነሳታቸውን በተግባር እያሳዩ ይገኛሉ።