የውጭ መገናኛ ብዙሃን የዓለምአቀፉ ማህበረሰብ እውነታውን እንዳይረዳ እንቅፋት ሆነዋል

162

ሐምሌ 22/2013 (ኢዜአ) የውጭ መገናኛ ብዙሃን የዓለምአቀፉ ማህበረሰብ እውነታውን እንዳይረዳ እንቅፋት ሆነዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናታን ተስፋዬ እና የአሀዱ ሬዲዮ ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛና ደራሲ ጥበቡ በለጠ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በኢትዮጵያ ላይ የተዛባና እውነታውን የማያሳይ መረጃዎች የሚያሰራጩ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ የአሸባሪውን የህወሓት ድርጊት እንዳይታወቅ እንቅፋት ሆነዋል።

የውጭ መገናኛ ብዙሃኑ አሸባሪው ህወሃት በሥልጣን በቆየባቸው ዓመታት ከኢትዮጵያ ህዝብ ዘርፎ በሰጣቸው ገንዘብ የተገዙ በመሆናቸው ለአንድ ወገን ብቻ እየሰሩ ናቸው።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናታን ተስፋዬ በትግራይ ክልል በነበረው የህግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ያሰራጩት ዘገባ ለአንድ ወገን ያደላ መሆኑ የዓለም ህዝብ እውነታውን እንዳያቅ እንቅፋት ሆነዋል።

በአሁኑ ወቅት የፌዴራል መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ካወጀ በኋላም እንኳን በእነዚህ  የውጭ መገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩ ዘገባዎች እውነታውን የማያሳዩ የተዛቡ መረጃዎች መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ህፃናትን ለውትድርና ሲጠቀም፤ በአማራና በአፋር ክልሎች ተሻግሮ ትንኮሳ ሲፈጽም እነዚህ መገናኛ ብዙሃን ምንም ነገር እንደማይሉ ነው ያብራሩት።

እነዚህ የውጪ መገናኛ ብዙሃን ለአሸባሪው ህወሃት እውቅና የሚሰጡና የኢትዮጵያን ህዝብና መንግስት ጫና ውስጥ የመክተት አጀንዳ ያላቸው መሆኑን ገልፀው፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እውነቱን እንዳይረዳ እንቅፋት ስለመሆናቸው ነው ያስረዱት።

የአሀዱ ሬዲዮ ስራ አስኪያጅ ጋዜጠኛና ደራሲ  ጥበቡ በለጠ በበኩላቸው እነዚህ መገናኛ ብዙሃን አጀንዳ አድርገው የሚንቀሳቀሱት ኢትዮጵያን ለማፍረስ አልያም አሸባሪውን ቡድን ወደ ስልጣን ለማምጣት ፍላጎት እንዳደረባቸው ይጠቁማሉ።

እነዚህ መገናኛ ብዙሃን አሸባሪው ህወሓት በስልጣን በነበረ ወቅት ከኢትዮጵያ ህዝብ ዘርፎ በወሰደው ገንዘብ በሚከፍላቸው ገንዘብ የተገዙ መሆኑን አመልክተው፤ አሁን ላይ የተዛቡ መረጃዎችን እያቀረቡ እንደሆነ እና ዓላማቸውም ኢትዮጵያን ማፍረስ መሆኑን ነው የሚናገሩት።

በስመ ጋዜጠኛና ተንታኝ እየተባሉ በመገናኛ ብዙሃን እየቀረቡ የሚናገሩ ሰዎች የቡድኑ ቅጥረኛ እና የቡድኑን አቋም ይዘው የሚያንፀባርቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እነዚህ የመገናኛ ብዙሃን አሸባሪው ቡድን የሚደግፉበት ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለው መንግስት የአፍሪካን ቀንድ የማስተሳሰር በጋራ የመልማት እና አፍሪካን ወደ ትብብር የማምጣት እንቅስቃሴ ምዕራባዊያንን በማስፈራቱ መሆኑን ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ መከፋፈሉ ቀርቶ  ወደ አንድነት መምጣት የምዕራባዊያንን ትኩረት መሳቡን አመልክተው፤  በእነርሱ የማትጠመዘዝ ኢትዮጵያ በማፍራት ከግስጋሴዋ ለማስቆም ፍላጎት ስላላቸው በመገናኛ ብዙሃናቸው አማካኝነት የተዛባ መረጃ እንዲቀርብ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ይህን ለመከላከል ኢትዮጵያዊያን ከምን ጊዜም በላይ በመንቃት አገር መጠበቅ እንደሚገባ የተናገሩት ሀሳብ ሰጪዎቹ፤ "የውጪ ተጽዕኖን ለመቋቋም በአንድነትና በህብረት መቆም ይገባናል" ብለዋል።

በመንግስት በኩል ያሉ የመረጃ አስጣጥ ክፍተቶች ሊታረሙ እንደሚገባ ጠቁመው፤ አገር አቀፍ የመረጃ ማዕከል አንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ከአፍ መፍቻ ቋንቋ ባሻገር የዓለም አቀፍ ቋንቋዎችን ተጠቅሞ ጫናዎችን መቀነስ እንደሚገባም ገልፀዋል።

በተለይም በማህበራዊ ትስስር ገፆች እያንዳንዱ ዜጋ ለኢትዮጵያ ዘብ በመቆም አሉታዊ ዘመቻዎችን በመመከት እውነታውን ማሳየት እንደሚጠበቅበት ተናግረው፤ ዜጎች ለኢትዮጵያ ድምጽ በመሆን የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም