ምዕራባዊያን ጥቅማቸው እንጂ ሠብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት አያሳስባቸውም - ዶክተር ደመቀ አጭሶ - ኢዜአ አማርኛ
ምዕራባዊያን ጥቅማቸው እንጂ ሠብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት አያሳስባቸውም - ዶክተር ደመቀ አጭሶ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 22 ቀን 2013 (ኢዜአ) ምዕራባዊያን ብሔራዊ ጥቅማቸውን ማስጠበቅ እንጂ ሠብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት አያሳስባቸውም ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህር ዶክተር ደመቀ አጭሶ ገለፁ።
በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ቆይታ ያደረጉት የፖለቲካል ሳይንስና ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህሩ ዶክተር ደመቀ አጭሶ በታሪክ ምዕራባዊያንና አሜሪካ ሠብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት አሳስቧቸው አገራትን አግዘውና ሰዎችን ከሞት አድነው አያውቁም ይላሉ።
በዓለምአቀፍ የዲፕሎማሲ ሕግ አገራት ከአገራት ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት ብሔራዊ ጥቅምን መሠረት ያደረገ ነው የሚሉት ዶክተር ደመቀ ይሁንና አሜሪካ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስጠብቅ ነገር ስታገኝ ሞትና መፈናቀል ግድ እንደማይሰጣት ነው የተናገሩት።
አገራቱ ብሔራዊ ጥቅሞቻቸው እስከተጠበቀ ድረስ በሙስናና በሠብዓዊ መብት ጥሰት ከሚተቹ አገራትና መንግሥታት ጋር ሲተባበሩ እንደነበረ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የምዕራባዊያኑን ጥቅም የሚያስጠብቅ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ቅድሚያ ሰጥቶ የሚሰራ ነው ያሉት ዶክተር ደመቀ "የትኛውም አገር ብሔራዊ ጥቅሙን እንደሚያስጠብቅ ሁሉ ኢትዮጵያም ብሔራዊ ጥቅሟን አስጠብቃ እየሰራች ነው" ብለዋል።
አገሪቷም በቀጣናዊ እና በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ኃያላን አገራት ጋር በሠላም ለመኖር ትክክለኛ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ቀርጻ እየሰራች ትገኛለች ነው ያሉት።
በተለይ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት በስኬት ማጠናቀቋ፤ ብሔራዊ ጥቅሟን ማስጠበቅ በሚያስችላት ደረጃ እየተንቀሳቀሰች መሆኗን ያመላከተ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የሚከውናቸው የልማትና የእድገት እንቅስቃሴዎች ስጋት የሆነባቸው ምዕራባዊያን በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።
እነዚህ አገራት ኢትዮጵያ ሉዓላዊት አገር መሆኗን ተረድተው መንግሥቷንና ሕዝቦቿን አክብረው መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም አክለዋል።
ኢትዮጵያዊያንም ከመንግሥት ጎን መቆምና እርስ በእርስ መደጋገፍ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።