ቀጥታ፡

ከጅግጅጋ ተነስቶ ወደ ድሬዳዋ ሲበር በነበረው አውሮፕላን ላይ የደረሰው አደጋ በጭጋጋማ አየር ሳቢያ የተከሰተ ነው - የኢትዮጵያ አውሮፕላን አደጋዎች ምርመራ ቢሮ

አዲስ አበባ ሃምሌ 21/2013 (ኢዜአ)  ከጅግጅጋ ተነስቶ ወደ ድሬዳዋ ሲበር በነበረው አውሮፕላን ላይ ትናንት የደረሰው አደጋ በጭጋጋማ አየር ሳቢያ የተከሰተ መሆኑን የኢትዮጵያ አውሮፕላን አደጋዎች ምርመራ ቢሮ አስታወቀ።

በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ አደጋ አለመኖሩን ቢሮው አረጋግጧል።

በትራንስፖርት ሚኒስቴር የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ቢሮ ጉዳዩን አስመልክቶ ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል።

የቢሮው ሃላፊ ኮሎኔል አምድዬ አያሌው የመጀመሪያ ምርመራ ውጤትን አስመልክተው እንደተናገሩት፤ ንብረትነቱ የአቢሲኒያ የበረራ አገልግሎቶች ድርጅት የሆነና የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኪራይ እየተገለገለበት የሚገኘው አውሮፕላን ትላንት ከቀኑ 7 ሰዓት ከ46 ደቂቃ ላይ አደጋ ደርሶበታል።

ሲሲና ካራቫን 208 ቢ ኢቲ የተባለው አውሮፕላን አደጋ የደረሰበት በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ሃረማያ ኮምቦልቻ ወረዳ ነው።

አውሮፕላኑ ከአዲስ አበባ ዋርዴር ጅግጅጋ በሰላም መብረሩን ያስታወሱት ሃላፊው፤ በ7 ሰዓት ከ13 ከጅግጅጋ ተነስቶ ወደ ድሬዳዋ እየበረረ ሳለ ከ33 ደቂቃ በኋላ አደጋው መከሰቱን አብራርተዋል።

አውሮፕላኑ በጭጋጋማ የአየር ሁኔታ ሳቢያ በአካባቢው ከነበረው መጠነኛ ተራራ ጋር ተጋጭቶ አደጋው መከሰቱን ተናግረዋል።

በአውሮፕላኑ ሁለት የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ሠራተኞችና ሁለት የበረራ ቡድን አባላት ተሳፍረው የነበረ ሲሆን፤ በተሳፋሪዎች ላይ ጉዳት አለመድረሱን በምርመራ መረጋገጡን አመልክተዋል። 

በቅድመ ምርመራ ሂደት አውሮፕላኑ በጭጋጋማ የአየር ሁኔታ ሳቢያ አደጋው እንደደረሰበት ቢታወቅም፤ ተጨማሪ የምርመራ ሥራ ለማከናወን የምርመራ ቡድን ወደ ስፍራው ማቅናቱ ተገልጿል።  

በአውሮፕላኑ ላይ የደረሰው አደጋ ከትግራይ ክልል ጋር ካለው ችግር እንደማይያያዝ ነው አቶ አምድዮ የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም