በአዲስ አበባ ሴቶችና ወጣቶች ደም በመለገስ ለመከላከያ ሠራዊት ያላቸውን ድጋፍ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ሴቶችና ወጣቶች ደም በመለገስ ለመከላከያ ሠራዊት ያላቸውን ድጋፍ ገለጹ
ሀምሌ 21/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ሴቶችና ወጣቶች ደም በመለገስ ለጀግናው መከላከያ ሠራዊት ያላቸውን ድጋፍ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለመከላከያ ሠራዊት ስንቅ በማዘጋጀት፣ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግና ደጀንነታቸውን በተግባር እያረጋገጡ ይገኛሉ።
ትናንትና በመስቀለ አደባባይ በተካሄደ "ኢትዮጵያን ለማዳን አዘምታለሁ!" በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው መርሃ ግብር ላይ ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ በመስጠትና ዘማች ወጣቶችን መርቆ በመሸኘት አሸባሪውን ህወሃትን ለማጥፋት በሚካሄደው ትገል የበኩሉን ሚና እየተወጣ ነው።
ዛሬ ደግሞ "ደማችን ለመከላከያችና ለአገራችን ኢትዮጵያ" በሚል መርህ የደም ልገሳ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በደም ልገሳ መርሃ ግብሩ የተሳተፉት ወይዘሮ አማረች አድማሱ፤ ለመከላከያ ሰራዊት በራስ ተነሳሽነት ደም መለገሳቸውን ተናግረዋል።፡
ለመከላከያ ሠራዊቱ ከዚህ በፊት ስንቅ በማዘጋጀትም ተሳትፎ ማድረጋቸውን አመልክተዋል፡፡
ወጣት አስናቀ ጋሻው በበኩሉ ለመከላከያ ሰራዊት ደም መለገሱ አጋርነቱን ለማሳየት ያደረገው ትንሹ ነገር መሆኑን ተናግሯል፡፡
ከዚህ ቀደም ደም መለገሱንና የአንድ ወር ደመወዙን መስጠቱን በመግለጽ በቀጣይም አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡
የክፍለ ከተማው ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ወንዳየሁ ደጀኔ በዚሁ ወቅት፤ የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች ለአገር መከላከያ ሠራዊት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠላቸውን ተናግረዋል ።
በዚህም ነዋሪዎቹ ቀደም ብለው ለመከላከያ ሠራዊት ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን ነው የጠቆሙት።
የክፍለ ከተማው ነዋሪ የሆኑ በርካታ ወጣቶች የመከላከያ ሰራዊቱን ለመቀላቀል ሽኝት እንደተደረገላቸውና በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ወንዳየሁ ገልጸዋል፡፡
ለሁለት ቀን በሚቆየው የደም ልገሳ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ዩኒት ደም ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል።