የመገናኛ ብዙሃን እርስ በርሳቸው ቁጥጥር የሚያደርጉበት ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል... ጥናት - ኢዜአ አማርኛ
የመገናኛ ብዙሃን እርስ በርሳቸው ቁጥጥር የሚያደርጉበት ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል... ጥናት
አዲስ አበባ፤ሃምሌ 21/2013(ኢዜአ) የመገናኛ ብዙሃን ባቋቋሙት ምክር ቤት አማካኝነት እርስ በእርሳቸው ቁጥጥር የሚያደርጉበት ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ የዘርፉን ተዋንያን ወደ መዋቅሩ ማስገባት እንደሚያስፈልግ አንድ ጥናት አመለከተ።
በመርሳ ሚዲያ የተሰራው "የመገናኛ ብዙሃን የርስ በርስ ቁጥጥር ተግባራዊ ማድረጊያ መንገድ በኢትዮጵያ" ጥናታዊ ጽሁፍ ለህትመት በቅቷል ።
በዓለም አቀፍ የሚዲያ ድጋፍ የፖሊሲና ልማት ባለሙያና የጥናቱ አዘጋጅ አቶ ሰለሞን ጎሹ እንዳሉት ፤ ጥናቱ ባለፈው አመት ከመገናኛ ብዙሃንና ከባለድርሻ አካላት ጋር የተደረጉ ውይይቶችን ጨምሮ በቃለ መጠይቅ የተሰበሰቡ ግኝቶች እና ቀጠናዊ ልምዶችን ያካተተ ነው።
መንግስት ህግና ፓሊሲ በማውጣት እየተገበረ ያለውን ቁጥጥር የዘርፉ ተዋንያን በራሳቸው የሙያ ደረጃ በማየት እርስ በእርስ የሚገማገሙበትን እና ውሳኔ በመስጠት የሚያጠናክሩበትን ሃሳብ ያካተተ እንደሆነም ተናግረዋል።
በመገናኛ ብዙሃን የጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ የእርስ በርስ ቁጥጥር ስርዓት ተግባራዊ አፈፃፀም እውን ሲሆን የሚገጥሙ ተግዳሮቶች እና ዕድሎችን እንደሚያብራራ ነው የተናገሩት።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ስለ መገናኛ ብዙሃን የእርስ በርስ ቁጥጥር፣ አመሰራረትና አተገባበር ለዘርፉ ባለሙያዎች ግንዛቤ መፍጠር እንዳለበት በጥናቱ መመላከቱን ተናግረዋል።
የእርስ በርስ ቁጥጥር ስርዓት ትግበራው ስኬታማ እንዲሆን እምነት የሚጣልበት መዋቅር መፍጠር እንደሚገባም ተጠቁሟል።
በዚህም ሙያዊ ብቃት ያለው፣ ስነ ምግባር የሚያከብር እና ሃላፊነት የሚሰማው ጋዜጠኛ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ነው የጠቆመው ።
ጥናቱ ለመገናኛ ብዙሃን የእርስ በርስ የመገማገሚያ እና ተጠያቂነት አሰራር ተግባራዊ ምላሽ የሚሰጥ አደረጃጀት እንደሚያስፈልግ ማመላከቱን ተናግረዋል ።
የጥናቱን ምክረ ሃሳብ ያቀረበችው ጋዜጠኛ ፋሲካ ታደሰ እንደተናገረችው፤ ጥናቱ መንግስት፡ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት፣ የመገናኛ ብዙሃን ማህበራት፣ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤትና ማሰልጠኛ ተቋማትና ለጋሽ ድርጅቶች ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው ያመላክታል።
ጥናቱ በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋ ለህትመት በቅቷል።
መርሳ የሚዲያ ተቋም ለትርፍ ያልተቋቋመ የሚዲያ ፖሊሲ፣ ምርምር ጥናት እና አቅም ግንባታ የሚሰጥ ተቋም ነው ።