ኮርፖሬሽኑ የአቅመ ደካሞችና ገቢያቸው ዝቅተኛ የሆኑ ዜጎችን የመኖሪያ ቤት እድሳት አስጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ኮርፖሬሽኑ የአቅመ ደካሞችና ገቢያቸው ዝቅተኛ የሆኑ ዜጎችን የመኖሪያ ቤት እድሳት አስጀመረ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 20 ቀን 2013 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በልደታ ክለፍ ከተማ የአቅመ ደካሞችና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች የመኖሪያ ቤት እድሳት አስጀምሯል፡፡
በእድሳት ማስጀመሪያው መርሃ-ግብር የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት፣ የተቋሙ የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም የግንባታ ስራ ተቋራጮች በጋራ እድሳቱን አስጀምረዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ በመዲናዋ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የኅብረተሰብ ክፍሎች መኖሪያ በማይመስሉ ቤቶች ውስጥ ተጠልለው እንደሚኖሩ ተናግረዋል።
ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ሁሉም አቅሙ በፈቀደ መልኩ በመተባበር መስራት ይገባል ብለዋል።
ኮርፖሬሽኑ የአቅመ ደካሞችን ቤቶች አፍርሶ መሥራት ከጀመረ ሦስት ዓመታትን እንዳስቆጠረና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
የቤቶች እድሳት መርሃ-ግብሩ በሁሉም ክፍለ ከተሞች እንደሚካሄድና የበጎ አድራጎት ሥራው አቅመ ደካማ ዜጎች ተመልካች ወገን እንዳላቸው እንዲያስቡ ከማድረግ ባሻገር ቀሪ ሕይወታቸውን በተሻለ እንዲመሩ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
እድሳቱ ከኮርፖሬሽኑ ጋር በጋራ ለመስራት ቃል ከገቡ ተቋራጮችና ማኅበራት በጎ ፈቃድ እንደሚከናወን ገልጸዋል።
የአቅመ ደካሞቹን መኖሪያ ቤቶች ለማደስ ቃል የገቡ የሥራ ተቋራጮችና ባለሃብቶችንም አመስግነዋል፡፡
ቤታቸው የሚታደስላቸው ወይዘሮ ወርቅነሽ አካሉ ላለፋት 40 ዓመታት በከፋ ችግርና ድህነት ውስጥ ይኖሩ እንደነበር ተናግረዋል።
እንጀራ ጋገራና የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ቤታቸውን ለመጠገን መጣራቸውን የሚናገሩት ወይዘሮዋ አሁን ከፍተኛ የጤና ችግር እንደገጠማቸውና ይህን ለማድረግ እንዳቃታቸው ገልጸዋል።
የእለት ጉርሳቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች እያካፈሏቸው እንደሚኖሩ ገልጸው፤ ቤታቸው ሊታደስላቸው በመሆኑ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
ወይዘሮ ወርቅነሽ ይህን መልካም ሥራ ለመሥራት የተነሳሱትን ሁሉ አመስግነዋል።