በሀገሪቱ 117 ከተሞች የተቀናጀ የልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ተጠቃሚ መሆናቸው ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በሀገሪቱ 117 ከተሞች የተቀናጀ የልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ተጠቃሚ መሆናቸው ተገለጸ
ጂንካ፤ ሐምሌ 20 /2013 (ኢዜአ) በሀገሪቱ ክልሎችና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ስር የሚገኙ 117 ከተሞች የተቀናጀ የልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ተጠቃሚ መሆናቸውን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ ሙሐመድ ገለጹ።
የፌደራል፣ክልሎችና የከተሞች ተቋማዊና መሰረተ-ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም የጋራ ክትትልና ድጋፍ ንቅናቄ የምክክር መድረክ በጂንካ ከተማ ተካሄዷል፡፡
ሚኒስትሯ በምክክር መድረኩ እንዳሉት፤ ከ2011 ዓ.ም፡ ጀምሮ በከተሞቹ ሲተገበር የቆየው የፕሮግራሙ ዓላማ የከተሞችን የማስፈፀም አቅም በማሳደግ ቀጣይነት ያለውና ዘላቂ መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት ነው።
የመንግስት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጅዎችን መሰረት አድርጎ በተቀረጸው ፕሮግራሙ የሴቶችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፣ሰፊ የስራ እድልና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገሩ ከተሞችን መፍጠር እንደሆነም አመላክተዋል።
በዚህም አዲስ የተዋቀረውን ሲዳማን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎችና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ስር የሚገኙ 117 ከተሞችን ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ስራው አሁንም በመቀጠል የፕሮግራሙ ዓመታዊ የካፒታል ኢንቨስትመንት እቅድ ስርዓተ ፆታ ማዕከል በማድረግ ህብረተሰቡን በቀበሌ ከተማ ደረጃ በማሳተፍ እየተተገበረ እንደሚገኝ ኢንጅነር አይሻ ተናግረዋል።
ፕሮግራሙ የሚካሄደው ከከተሞችና ክልሎች ከሚዋጣው የተዘማጅ በጀት በተጨማሪ ከልማት አጋሮች የሚገኝ የፋይናነስ ወጪ በጀት ነው ብለዋል።
በሚኒስቴሩ የከተሞች ገቢ ማስፋፊያ ፈንድ ሞብላይዜሽን የፋይናንስ ቢሮ ሀላፊና የፕሮግራሙ አስተባባሪ አቶ ባምላኩ አዳሙ በበኩላቸው፣በተመረጡ ከተሞች ሲካሄድ የቆየው ፕሮግራሙ የሚጠናቀቅበት ጊዜ እየተቃረበ መምጣቱን ተናግረዋል።
የጂንካው መድረክ በትግበራው ወቅት ክፍተቶችን እና ጥንካሬዎችን በመለየት በቀሪ ጊዜያት የፕሮግራሙን ዓላማ ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት እንዲቻል መግባባት ላይ ለመድረስ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በአፈፃፀም ግምገማው መሰረት የፕሮግራሙ ተጠቃሚ ከተሞች አበረታች ለውጦች እየታዩ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በሁሉም ከተሞች በአፈፃፀም ወቅት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና የመፍትሄት እርምጃዎችን በመውሰድ በሚሰሩ ፕሮጀክቶች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል፡፡
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የአማራ ክልል የፕሮግራሙ አስተባባሪ አሻግሬ አቤልነህ በሰጡት አስተያየት ፤ ፕሮግራሙ በክልሉ 32 ከተሞች እየተፈጸሙ ያለ መሆኑን ተናግረዋል።
ከፕሮግራሙ ሰራዎች መካከል የድንጋይ ንጣፍና ጠጠር መንገድ፣ የተፋሰስና አረንጓዴ ልማት እንደሚገኙበት ጠቀሰው በእስካሁኑ ሂደት አፈጻጸሙ አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ክልል የፕሮግራሙ አስተባባሪ አቶ አምሳሉ ደሳለኝ በበኩላቸው፤ ፕሮግራሙ በክልሉ 38 ከተሞች ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ሲካሄድ መቆየቱንና በተለያዩ የልማት መስኮች አፈጻጻሙ እየተሻሻለ ከክልሉና ከልማት አጋሮች የሚመደበው በጀት እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
የማስፈሚያ ዓመታዊ በጀቱ 900 ሚሊዮን የነበረው ባለፈው የበጀት ዓመት ወደ 3 ቢሊዮን ብር ከፍ ማለቱን አመላክተዋል።
በሱማሌ ክልል ባለፉት ሶሰት ዓመታት በተለያዩ ከተሞች በፕሮግራሙ በተገኘው ድጋፍ ውጤታማ የሆኑ የመሰረተ ልማትና የአደረጃጀት አቅም ግንባታ ተግባራት መከናወናቸውን የገለጹት ደግሞ በከልሉ የፕሮግራሙ አሰተባባሪ አቶ ሰመትር ፈለቀ ናቸው። .
የጂንካ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ታዬ ገንማይ በበኩላቸው፤ የ70 ዓመት እድሜ ያለው ጂንካ ከተማ ከማዕከሉ ባለው ርቀት እና በመዋቅር ኢ-ፍትሃዊነት ሳቢያ እድገቱ የእድሜውን ያህል አይደለም ብለዋል።
በፕሮግራም ተካቶ ወደ ሥራ ከገባበት ጊዜ አንስቶ ለውጦች እየታዩ መሆኑንና በዚህም ለውጥ ካመጡ የሀገሪቱ ከተሞች ጂንካ አንዱ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በመድረኩ በፕሮግራሙ ተጠቃሚ የሆኑ ከተሞች የሶስት ዓመታት የአፈፃፀም ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን እስከ 2015 የሚቆየው ፕሮግራሙ በቀሪው ጊዜያት መሰራት ያለባቸው ተግባራትም ተለይተው ለመፈጸም መግባባት ላይ ተደርሷል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማት፣ኮንስትራክሽን እና የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አሸናፊ ጋኢሚን ጨምሮ ሌሎችም የፌደራል ፣ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የፕሮግራም አስተባባሪዎችና የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት በመድረኩ ተሳትፈዋል፡፡
በጂንካ ከተማ በፕሮግራሙ የተከናወኑ የልማት ስራዎች በተሳታፊዎቹ መጎብኘታቸውን የኢዜአ ሪፖርተር ከሥፍራው ዘግቧል፡፡