በጋምቤላ ክልል በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የነበሩ ፈተናዎችን በመቋቋም አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል- አቶ ኡሞድ ኡጁሉ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የነበሩ ፈተናዎችን በመቋቋም አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል- አቶ ኡሞድ ኡጁሉ
ጋምቤላ ፤ ሐምሌ 20 /2013 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ዓመት የነበሩ ፈተናዎችን በመቋቋም በማህበራዊና ኢኖሚዊ ዘርፎች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አስታወቁ።
ርዕሰ መስተዳድሩ ጋምቤላ ከተማ እየተካሄደ ላለው የክልሉ ምክር ቤት 12ኛ መደበኛ ጉባዔ ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለጹት ባለፈው የበጀት ዓመት በተለይ በማዕድን ልማት፣ በገቢ አሰባሰብና በትምህርት ዘርፎች ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል።
በማዕድን ዘርፉ 1 ሺህ 200 ኪሎ ግራም ወርቅ በባህላዊ አምራቾች ለማምረት ታቅዶ 1 ሺህ 213 ኪሎ ግራም ተመርቶ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገቢ መደረጉን ጠቅሰዋል።
በበጀት ዓመቱ የተገኘው ወርቅ ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ948 ኪሎ ግራም ብልጫ እንዳለው ጠቁመው፤ከዚህም ገቢ ከ94 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ዶላር በላይ ማግኘት መቻሉን አሰታውቀዋል።
ከተለያዩ ግብር ገቢ ምንጮች ለመሰብሰብ ከታቀደው ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ውስጥ ከ95 በመቶ በላይ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል።
ገቢው ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከ397 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው ርዕሰ መስተዳድሩ አመላክተዋልል።
የኮሮና ወረርሽኝ በመቋቋም በቅድመ መደበኛ፣ መጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ተደራሽነት በማረጋገጥ ረገድ አበረታች ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
በግብርና ዘርፍም ባለፈው ክረምት በጎርፍ የወደመውን ሰብል በበጋው የግብርና ልማት ለማካካስ የተከናወኑት ሥራዎች መልካም ውጤት እንደተገኘባቸው በሪፖርታቸው አመላክተዋል።
የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ የተገኘው ውጤትም እንዲሁ።
የኮሮና ወረርሽኝ በመከላከልና የእናቶችና ህፃናት የጤና አገልግሎት በማሻሻል ረገድ የተከናወኑ ተግባራት መልካም አፈጻጸም እንደነባራቸው ተናግረዋል።
ሆኖም በኮሮና ወርርሽኝና ሌሎች ፈተናዎች ጋር ተያይዞ በክልሉ ከፍተኛ የዋጋ ንረት መታየቱን ርዕሰ መስተዳደሩ አብራርተዋል።
ከምክር ቤቱ አባላት መካከል አቶ ቲቶ ሐዋርያት በሰጡት አስተያየት፤ በክልሉ እየተስፋፋ የመጣው የኤች አይ ቪ/ ኤድስ ስርጭት ለመከላከል የተከናወኑት ሥራዎች ውስንነት ታይቶባቸዋል ብለዋል።
ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የክልሉ የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና ጥራት እንዲከናወኑ በማድረግ በኩል የሚታዩ ክፍተቶች እንዲታረሙ ያመለከቱት ደግሞ ሌላው የምክር ቤት አባል አቶ ኦኬሎ አማን ናቸው።
ርዕሰ መስተዳድሩ ለጥያቄዎቹ በሰጡት ምላሽ ቢሮዎች ባለፈው በጀት ዓመት ኤች አይ ቪ/ ቫይረስን ስርጭት መከላከል ከመደበኛ ዕቅዳቸው ጋር አካተው እንዲሰሩ መደረጉን አስታውሰዋል።
የልማት ፕሮጀክቶች በግንባታ ግብዓቶች የዋጋ መጨመር ምክንያት መዘግየት የሚታይባቸው ቢሆንም፤ጥራታቸውን ለማስጠበቅ ግን የተጠናከረ ክትትል እንደሚደረግ ገልጸዋል።
ጉባዔው በዛሬ ውሎው የተጠናቀቀውን በጀት ዓመት የልማትና የመልካም አስተዳደር፣የኦዲትና የጠቅላይ ፍርድ ቤት የሥራ ክንውን ሪፖርቶችን አዳምጦ አጽድቋል።