የደቡብ ክልል ለመከላከያ ሠራዊት የእርድ ሰንጋዎች፣ በግና ፍየሎችን አበረከተ - ኢዜአ አማርኛ
የደቡብ ክልል ለመከላከያ ሠራዊት የእርድ ሰንጋዎች፣ በግና ፍየሎችን አበረከተ
ሐምሌ 20/2013 (ኢዜአ) የደቡብ ክልል የተለያዩ ዞኖች ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ እንዲውል ሰንጋዎች፣ በግና ፍየሎችን ዛሬ አበረከቱ።
በክልል ደረጃ 250 ሚሊዮን ብር የማሰባሰብ ንቅናቄ መጀመሩም ተገልጿል።
የክልሉ ተወካዮች ዛሬ ጦር ኃይሎች በሚገኘው ምድር ኃይል 155 የእርድ ሰንጋዎች፣ 399 በግና ፍየሎች፣ እንዲሁም የታሸገ ውሃና የተለያዩ የምግብ አይነቶችን አስረክበዋል።
የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰማን ሺፋ የክልሉ ሕዝብ ለመከላከያ ሠራዊቱ ከ37 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመዋል።
በክልል ደረጃ በአይነትና በጥሬ ገንዘብ 250 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ መታቀዱንና ይህም ይሳካ ዘንድ በዞን፣ በወረዳ፣ በልዩ ወረዳና በከተሞች ንቅናቄ መጀመሩን ገልጸዋል።
የስልጤ ዞን ብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊና የመከላከያ ሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አብዱራህማን ወርቅቾ በዞኑ ለሠራዊቱ 8 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ ታቅዶ እንደነበር አስታውሰዋል።
ይሁንና በሕዝቡ መነሳሳት ከታቀደው በላይ 10 ሚሊዮን 961 ሺህ ብር ማሰባሰቡን ተናግረዋል።