የሴቶችን የሠላም ወዳድነት እሳቤ ለዘላቂ ሠላም ግንባታ መጠቀም ይገባል

126

ሐምሌ 20/2013 (ኢዜአ)  በኢትዮጵያ ሴቶች በማኅበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን ሠላም ወዳድነት እሳቤ ለዘላቂ ሠላም ግንባታ መጠቀም እንደሚገባ ተጠቆመ።
የደህንነት ጥናትና ምርምር ተቋም ከሠላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር "ሴቶች በኢትዮጵያ በግጭት ወቅት እንደ ተጎጂ እና ጀግኖች" በሚል የውይይት መድረክ አካሂዷል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ የመንግሥት ሥርዓቶች በነበሩ ግጭቶች ሴቶች የደረሰባቸው ጉዳት፣ ግጭቶችን ለመፍታት የተጠቀሙበት ብልሃት የተሞላበት አካሄድና በሚጠቀሙባቸው ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች ላይ ያጠነጠኑ የውይይት መነሻ ጽሑፎች በምሁራን ቀርበዋል።

ኢትዮጵያዊያን ሴቶች በተለያዩ የመንግስት ሥርዓቶች በተከሰቱ ግጭቶች ቀዳሚ ተጎጂ ቢሆኑም ግጭቶችን ለማብረድ የተጠቀሙባቸውን ጥበብ የተሞላባቸው አካሄዶችም ፅሁፍ አቅራቢዎቹ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያኑ ሴቶች እንደየአካባቢያቸው ከሚጠቀሙባቸው ባሕላዊ የግጭት አፈታቶች መካከል ሴቶች "አደ ስንቄና" ሌሎችም ዘዴዎችን ለሠላም እንደሚጠቀሙ ጨምረዋል።

በዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ ሴቶች ለሠላም ግንባታ ያበረከቱትን አስተዋጽኦና አሁን ያለውን ሁኔታ የሚዳስስ ጽሑፍ ያቀረቡት የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያ ጸባኦት መላኩ ተንትነዋል።

በግጭት ወቅት ቤተሰብን ከመበተን በመታደግ፣ የግጭት አፈታት የመፍትሔ ሐሳቦችን በማፍለቅ፣ የአገርን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ጦርነቶች ሲከሰቱ በጦርነቱ በመሳተፍና ስንቅ በማዘጋጀት ያላቸውን ሚና ዘርዝረዋል።

በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚሰጣቸውን ሠላም ወዳድነትና ተንከባካቢነት ወደ መድረክ በማምጣት ለግጭት አፈታት መጠቀም እንደሚቻልም መክረዋል።

በደህንነት ጥናትና ምርምር ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ሰሚር የሱፍ ሴቶች ባላቸው ምጣኔ ሃብትና የፖለቲካ ደረጃ በግጭት ወቅት ይበልጥ ተጎጂ እንደሚሆኑ ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጂ የግጭት ወቅት ተጎጂ ብቻ ሳይሆኑ ዘላቂ ሠላም ለማምጣት ያላቸውም ሚና ከፍተኛ መሆኑን ነው ያስረዱት።

የሠላም ሚኒስትሯ አማካሪና የብሔራዊ መግባባትና ማኅበራዊ ሃብት ግንባታ ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ ሚናስ ፍስሃ በበኩላቸው፤ መንግሥት ዘላቂ ሠላም ለማምጣት ከሚከውነው ተግባር አንዱ ሴቶችን ያሳተፉ መድረኮች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሴቶች በሠላም ግንባታ በተለያዩ አካባቢዎች ያላቸውን ሚና ከግምት በማስገባት ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት ማኅበረሰቡን የማንቃት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።

በውይይት መድረኩ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ተመራማሪዎች፣ የመንግሥት ተወካዮችና እንግዶች የታደሙ ሲሆን በቀረቡ ጽሑፎች ላይ ሐሳቦች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም