ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር ቁርጠኞች ነን - ዘማች ወጣቶች

 ሐምሌ 20/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር ሲባል አሸባሪውን ህወሃት ለመደምሰስ በሚደረገው ትግል በቁርጠኝነት መሰማራታቸውን ዘማች ወጣቶች ገለፁ።

አሸባሪው ህወሓት በአገር ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ትናንት ባቀረቡት ጥሪ መሰረት ከሦሰት ሺ በላይ የከተማዋ ወጣቶች ምላሽ ሰተዋል።

በዚህም የአገር መከላከያ ሰራዊትን ለመቀላቀል የወሰኑ ወጣቶች በዛሬው ዕለት በመስቀል አደባባይ አሸኛኘት ተደርጎላቸዋል።

በዚህ ወቅት አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ወጣቶች መካከል ኢትዮጵያዊነት ማለት በአብሮነት፣ የወደፊት ነፃነትን አስከብሮ፣ በጋራ ለማደግ የመስማማት ውጤት ስለመሆኑ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን የቀደሙ አባቶችና እናቶች በደምና መስዋዕትነት ለትውልዱ ማስረከባቸውን ጠቁመው፤ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመድፈር የሚቃጣ ማንኛውንም የውስጥም ሆነ የውጪ ሀይል ለመመከት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ  "ማንም ተነስቶ የሰራት አይደለችም፤ ማንም ማፍረስ አይችልም" ያሉት ወጣቶቹ፤ በአባቶች ደምና አጥንት የተገነባችው አገር "ዛሬ በወጣቶች ደምና አጥንት ታፍራና ተከብራ ትኖራለች" ብለዋል።

ይህን የኢትዮጵያዊያን አብሮነትና አንድነት ለመናድና ለውጪ ወራሪዎች አሳልፎ ለመስጠት የሚሰራውን አሸባሪው ህወሓትን ለመደምሰስ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልፀዋል።

"ኢትዮጵያዊ ማንነታችንን የማስከበር ግዴታ አለብን" የሚሉት ወጣቶቹ፤ አገር በማንም አሸባሪ ቡድን ሆነ የውጪ ወራሪ ሀይል እንደማትደፈር ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን ጥፋት "ወጣቶች በጋራ ቆመን እንመክታለን" ሲሉ አረጋግጠዋል።

ወጣቶቹ ከኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ጎን በመቆም አሸባሪውን ህወሓት ለመደምሰስ እና ከውስጥም ሆነ ከውጪ ኢትዮጵያን ለማዳከም የተሸረበውን ሴራ ለማክሸፍ የቀደሙ አባቶችን ወኔ በመላበስ የኢትዮጵያን ጠላቶች እንደሚመክቱ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም