ቀጥታ፡

ህወሃት የሚታወቅበት ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትና አገር የማፍረስ ሴራ በህዝብ ትግል ይወገዳል ….አቶ አብርሃም አለኸኝ

ባህር ዳር ሐምሌ 20/2013 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት የሚታወቅበትን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትና አገር የማፍረስ ሴራ ለማስቆም ለቀረበው የክተት ጥሪ ከወጣቶች የተሰጠው ፈጣን ምላሽ በድል እንደሚጠናቀቅ በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

 የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አብርሃም አለኸኝ ዛሬ በሰጡት መግልጫ አሸባሪው ትህነግ መንግስት በተናጥል ያስተላለፈውን የተኩስ አቁም ለጥፋት ዓላማ በመጠቀም በአማራና በአፋር ክልሎች ወረራ እያካሄደ ይገኛል።

የወረራው ዋና ዓላማም ኢትዮጵያን ማፈራረስ፣ ህዝብን ማጎሳቆልና አማራን ከምድረ ገጽ ማጥፋት መሆኑን በቃል ከሚናገረው ውጭ በደረሰባቸው አካባቢዎች በፈጸመው ድርጊት መረጋገጡን ገልጸዋል።

ባካሄደው ወረራ አሸባሪው ልዩ ሃይሉና ሌላው ታጣቂ እያለቀ ቢመጣበትም ህጻናትን፣ እናቶችንና አዛውንቶችን እንደ ሽፋን በመጠቀም ለጦርነት ማግዶ እያስጨረስ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

አሸባሪው ቡድኑ በደረሰበት ቦታ ሁሉ የአርሶ አደሩን ጎተራ፣ የበሰለ ምግብና የተፈጨ ዱቄት በመዝረፍ፣ ሴት ህጻናትንም በመድፈርና በመግደል አሰቃቂ ወንጀሎችን እየፈጸመ እንደሚገኝ አቶ አብርሃም አስረድተዋል።

"የመከላከያ ሠራዊታችን፣ ልዩ ሃይሉ፣ ሚሊሻውና ሌላው ወደ ግንባር የዘመተው ሃይል በጽናት በመፋለም የአሸባሪውን እኩይ ሴራ እያመከነ ይገኛል" ብለዋል።

ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተነሳውን የጋራ ጠላት ከሁሉም ክልሎች የመጡ የልዩ ሃይል አባላት በጽናት እየተፋለሙት በመሆኑ ጽሕፈት ቤታቸው ትልቅ አክበሮት እንዳለውም ነው የገለጹት።

በአሁኑ ወቅት የአማራ ክልል መንግስት ያቀረበውን የክተት ዘመቻ ጥሪ ተከትሎ የመንግስትና የግል ትጥቅ ያላቸው ግለሰቦች ወደ ወረዳ ማዕከላት በመሰባሰብ ዝግጁነታቸውን ማሳየታቸው የሚያኮራ መሆኑንም አቶ አብርሃም ተናግረዋል።

የክልሉ ወጣቶችም በየአካባቢያቸው በመመዝገብና ወደ ስልጠና በመግባት ክልሉን ብሎም ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የመጣውን አሸባሪ ቡድን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት አኩሪ ምላሽ መስጠታቸው እንደሚደነቅም ገልጸዋል።

ሃላፊው እንዳሉት የአማራ ህዝብ ሁሉም ወደ ግንባር በመትመም አሸባሪውን ቡድን መግቢያና መውጫ በማሳጣት ለህልውናው አስፈላጊውን መስዋዕትነት መክፈል ይኖርበታል።

"የገጠመን የህልውና አደጋ በመሆኑ ህዝቡ በጉልበቱ፣ በገንዘቡ፣ በእውቀቱና በሚችለው ሁሉ በአንድነት በመሰለፍ አሸባሪውን ጁንታ መደምሰስ” ይገባል ያሉት አቶ አለኸኝ ወጣቱ የአባቶችን የጀግንነት ታሪክ እንደሚደግምም ተናግረዋል።

"አሸባሪው ቡድን እድል ካገኘ ኢትዮጵያን ከማፈራረስ ወደ ኋላ አይልም" ያሉት አቶ አብርሃም፣ የህልውና ትግሉ ምክንያታዊና ፍትሃዊ በመሆኑ በአሸናፊነት እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል።

የክልሉ ህዝብ፣ ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በአንድነትና በጽናት በመሰለፍ በጀግኖች አባቶች መንገድ በመጓዝ ድል ማስመዝገብ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የክልሉ ህዝብም ስንቅና ትጥቅ በማቅረብ ትግሉ ባጭር ጊዜ በድል እንዲጠናቀቅ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ እንዲያጠናክርም አሳስበዋል።

የአማራ ክልልን ጨምሮ በመላው ሃገሪቱ የሚገኙ የጸጥታ አካላትና ዜጎች ሃገር የማዳን ዘመቻውን በመቀላቀል ከሃገር መከላከያ ሰራዊት ጎን መሰለፋቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም