ቀጥታ፡

የሰመራ ከተማ ነዋሪዎች ለሠራዊቱ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ምግብ-ነክ ቁሶች ድጋፍ አደረጉ

ሰመራ ፤ ሐምሌ 20 /2013(ኢዜአ) በአፋር ክልል የሰመራ ከተማ ሕዝብና ተቋማት ለሀገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ከ4ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ምግብ-ነክ ቁሶች ትላንት ድጋፍ ማድረጋቸውን የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው ሃላፊና የዘመቻው የሀብት አሰባሳቢ ዓቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መሐመድ ሐሰን እንዳስታወቁት፤ ከድጋፉ ውስጥ  የከተማዋ ነዋሪ ሕዝብ  አስተዋጽኦ 2ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሲሆን ቀሪው የተቋማት ድርሻ ነው።

ከድጋፉም  428 ኩንታል ዱቄት፣ 10 ኩንታል ስኳር፣  1ሺህ 100 ደርዘን የታሸገ ውሃና 360 ካርቶን ብስኩት ይገኙበታል።


በቀጣይም በየደረጃው የሚገኙ የክልሉን የአስተዳደር እርከኖችና የሕዝቡ ድጋፍ የሚያስተባብር ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ሥራ እየገባ መሆኑን ገልጸዋል።

አሸባሪውን የህወሓት ቡድን የጥፋት ተልዕኮ ለማክሸፍ ለተሰማሩት የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣የክልሎች ልዩ ሃይሎችና ሚሊሺያዎች የገንዘብና ምግብ ነክ ድጋፍ በመደረግ ላይ እንደሚገኝ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም