ህዳሴ ግድብ ሃገራዊ አንድነትን የፈጠረ ፕሮጀክት ነው - ግራሃም ፒብልስ - ኢዜአ አማርኛ
ህዳሴ ግድብ ሃገራዊ አንድነትን የፈጠረ ፕሮጀክት ነው - ግራሃም ፒብልስ
ሀምሌ 20/2013 ( ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መላው ኢትዮጵያውያንን በአንድነት ያስተሳሰረ ፕሮጀክት መሆኑን ግርሃም ፒብልስ የተባሉ ጸሃፊ ገለጹ።
በኢትዮጵያ ያለው አብዛኛው የገጠር ነዋሪ ከኤሌክትሪክና መሰል መሰረተ ልማቶች የራቀ ከመሆኑም በላይ ድርቅና የጎርፍ አደጋዎች የሚያስከትላቸውን ችግሮች እየተጋፈጠ ለመኖር መገደዱን ጸሃፊው ‘ዲሲደንት ቮይስ ‘ ለተባለው ድረገጽ ገልጸዋል።
እነዚህን ችግሮች ለማሰወገድ ከ1950ዎቹ ጀምሮ ሲታሰብ የቆየው የሃይል ዘርፍ ማስፋፊያ ከአስር አመታት በፊት ተግባራዊ መሆን ጀምሮ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ለህዝቡ መበሰሩን ጠቅሰዋል።
ጸሃፊው ከጅምሩ አንስቶ ከአፍሪካ ግዙፍ የሆነውን የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከሱዳንና ግብጽ መሪዎች ባለፈም አሜሪካ እንግሊዝና ተባባሪዎቻቸውም እንዳልፈለጉት የሚያሳዩ በርካታ ተግባራትን ሲፈጽሙ መቆየታቸውን አንስተዋል።
የግብጽና የሱዳን መሪዎች ከወንዙ አንዲት ጠብታ ውሃ ብትነካ ወታደራዊ እርምጃ እንወስዳለን ማለት ከጀመሩ መሰንበታቸውን አስታውሰዋል።
ግድቡ የጎላ ጉዳት እንደማያስከትል በአለምአቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ማረጋገጫ ቢሰጥበትም እውነታውን መቀበል ያልፈለጉት ግብጽና ሱዳን አሁንም የቅኝ ግዛት ዘመን ውሎችን መከራከሪያ አድርገው በማቅረብ ላይ ናቸው ብለዋል ።
ህጋዊና አሳሪ ስምምንት እንዲኖር የሚወተውቱት ሃገራቱ በአረብ ሊግ ገፋፊነት ጉዳዩን ከአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በመውሰድ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት እንዲያመራ ቢያደርጉም ያሰቡትን ማግኘት እንዳልቻሉ ገልጸዋል ።
አሁን ግድቡ ለኢትዮጵያውያን ከምንም በላይ አስፈላጊነቱ እየጨመረ የመጣ ሲሆን ሲጠናቀቅ ከሚያቀርበው የኤሌክትሪክ ሃይል በተጨማሪ በአካባቢው ለሚኖሩ ሰዎች ንጹህ የመጠጥ ውሃ የመጓጓዣ አማራጭ እንዲሁም ለአነስተኛ መስኖ የሚሆን ትሩፋት እንዳለው አብራርተዋል።
የደኖች መጨፍጨፍን በማስቀረት ንጹህ አየር እንዲኖር የሚያደርግ የተስተካከለ የውሃ ፍሰት የሚፈጥርና የሴቶችን የስራ ጫና የሚቀንስ መሆኑንም አስረድተዋል።
የግድቡ ግንባታ ለኢትዮጵያውያን አንደኛው የህብረትና የኩራት ምክንያት ሆኖ መዝለቅ እንደቻለ ያብራሩት ጸሃፊው ኢትዮጵያ እንድትበለጽግና አቅሟን እንድታሳድግና የአፍሪካ ትንሳኤ ምልክት እንድትሆን የማትፈልገው ግብጽ ብቻ ሳትሆን አጋሮቿ ምእራባውያንም ግንባታውን ለማጓተትና ውስጣዊ ሰላሟን ለማደፍረስ እየጣሩ ነው ብለዋል።
በእነዚህ ሁሉ አጣብቂኞች መካከል ኢትዮጵያ ሰላማዊ ምርጫ ከማድረጓም በላይ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የተፈናቀሉ በርካታ ሚሊዮን ዜጎቿን መልሳ ለማቋቋም ጥረት እያደረገች መሆኑ ሊመሰከርላት እንደሚገባ ጸሃፊው አንስተዋል።