የዓለም ማህበረሰብ ህጻናትን ለጦርነት የሚማግደውን ህወሓት ሊያወግዘው ይገባል-የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር

2048

ሐዋሳ፣ ሐምሌ 19/2013 (ኢዜአ) ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪው ህወሓት ህጻናትን ለጦርነት በማሰለፍ እየማገደ ያለውን ተግባር እንዲያወግዝ የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ጠየቀ።

መንግሥት ለትግራይ ህዝብ የጽሞና ጊዜ በመስጠት የተናጠል ተኩስ አቁም ቢያውጅም ጁንታው ትንኮሳውን ወደ አጎራባች ክልሎች በማስፋት በጥፋት ተግባሩ የቀጠለ በመሆኑ ሊወገዝ እንደሚገባም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።


የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙና አህመድ ለኢዜአ እንደገለጹት አሸባሪው የህወሀት ቡድን ዓለም አቀፍ ሕጎችና ስምምነቶችን በመጣስ አደንዛዥ ዕጾችን በመስጠት ህጻናትን ለጦርነት በመማገድ ወንጀል እየፈጸመ ይገኛል።

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የተቀመጡ መብቶችም ቢሆኑ የሕጻናት መብቶች እንዲከበሩ እንጂ የጦር ሜዳ ተዋንያን እንዲሆኑ እንደማይፈቅዱ አመልክተዋል።

“ህጻናት የነገ ተስፋቸውን በሚያዩበት ዕድሜያቸው የጦርነት ሲሳይ ሊሆኑ አይገባቸውም” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ አሸባሪው ቡድን ህጻናትን በጦር ሜዳ በማሰለፍ  የሚፈጽመውን ድርጊት ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እንዲያወግዘው ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብም አሸባሪው ቡድን የህጻናትን ሰብዓዊ መብት በመርገጥ እየፈጸመ ያለውን ድርጊት እንዲቃወም አሳስበው የትግራይ እናቶችና ወላጆችም ለህጻናት የማይራራውን ጨካኝ ቡድን ተግባር እንዲያበቃ ማድረግ እንደሚገባቸው ነው ያመለከቱት።

አክለውም የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ግለሰቦችም ድርጊቱን ማውገዝና ማጋለጥ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

በወላይታ ዞን የኪንዶ ኮይሻ ወረዳ የሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ላቀች ለማ በበኩላቸው አሸባሪው  የህወሀት ቡድን ህጻናትን ለጦርነት በመማገድ እየፈጸመ ያለው ግፍ በአፋጣኝ መቆም እንዳለበት አመልክተው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሳፋሪ ድርጊት እየፈጸመ ባለው የህወሀት ቡድን ላይ ተገቢና አስተማሪ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ተናግረዋል።


“የትግራይ እናቶች የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬ የሆኑ ህጻናትን ወደ ጦርነት እየማገደ ያለውን ሽብርተኛ ቡድን በማውገዝ ልጆቻቸውን ከጥቃት ሊጠብቁ  ይገባል”  ሲሉ  መክረዋል።

የወላይታ ዞን ህጻናት ፓርላማ ዋና አፈ ጉባዔ ህጻን ተስፋነሽ ከተማ ህጻናት በለጋ ዕድሜያቸው መማርና ሰብአዊ መብታቸው ተከብሮ ከጦርነትና ጉልበታቸውን ከሚበዘብዙ ድርጊቶች ተጠብቀው ማደግ እንደሚገባቸው ትናግራለች።


“በተለይ የነገ ህይወታቸውን አደጋ ላይ የሚጥል የጦር መሳሪያ ማንገብ በዓለም አቀፍ ሕጎች ቢከለከልም በተቃራኒው አሸባሪው ቡድን ህጻናትን ለጦርነት በመማገድ የሚፈጽመውን አሳዛኝና አሳፋሪ ድርጊት እንቃወማለን” ብላለች።


በዓለም አቀፍ ደረጃ የህጻናት መብት ለማስከበር የሚንቀሳቀሱ አካላት ድርጊቱን እንዲያወግዙ ጠይቃለች።


“ህጻናት በለጋ ዕድሜያቸው በጦርነትና በሽብር ተግባራት ሳይታወኩ ትምህርታቸውን መከታተል  ይጠበቅባቸዋል” ያለው ደግሞ  በወላይታ ሶዶ ከተማ የጮራ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ5ኛ ክፍል ተማሪው ኤፍሬም ማቴዎስ ነው።


“በህጻናት ላይ የሚፈጸም የትኛውም ኢ-ሰብአዊ ድርጊት መወገዝና እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል” በማለት መልዕክት አስተላልፏል።