በኢትዮጵያ የዲጂታል ምጣኔ ሃብት ግንባታ ላይ የሳይበር ጥቃት እንዳይደርስ የ24 ሰዓት ጥበቃ እያደረግን ነው---ኢመደኤ

97

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19 ቀን 2013  (ኢዜአ) ኢትዮጵያ እያከናወነችው ባለው የዲጂታል ምጣኔ ሃብት ግንባታ ላይ የሳይበር ጥቃት እንዳይደርስ የ24 ሰዓት ጥበቃ እያደረገ መሆኑን የኢንፎርሜሽንና መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አስታወቀ። 
ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገቷን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ 'ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025' ስትራቴጂ ቀርጻ ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች።

በዚህም የገንዘብ ክፍያ፣ መረጃ ልውውጥና ሌሎች ተያያዥ ተግባራት በቴክኖሎጂ በመታገዝ እየተከናወኑ ሲሆኑ፤ የኢንፎርሜሽንና መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በዲጂታል አሰራሮች ላይ የሳይበር ጥቃት እንዳይደርስ ጥብቅ ክትትልና ጥበቃ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው ለኢዜአ እንዳሉት፤ የዲጂታል ምጣኔ ሃብት ግንባታ በዋናነት ከመረጃና የመረጃ መሰረተ ልማት ጋር የሚያያዝ በመሆኑ ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭነቱ ሰፊ ነው።

ኤጀንሲው ይህንን ታሳቢ በማድረግ የአገር አቀፍ ሳይበር ደህንነት አስተዳደር ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀርጾ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ዋና ዳሬክተሩ ገለጻ፤ የሳይበር ደህንነት አሰራሮች ውጤታማ የሚሆኑት በዘርፉ በሰለጠነ የሰው ኃይልና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዘው ተግባራዊ ሲሆኑ ነው።  

በተጨማሪም አሰራሮቹ ከውስን ተቋማት ባለፈ በአገር አቀፍ ደረጃ መተግበር ሲችሉ መሆኑንም ነው ያነሱት።  

ከዚህ አኳያ ኤጀንሲው ከውጭ ኢዲት ተደርገው የገቡ፣ እሴት የተጨመረባቸውና በአገር ውስጥ የበለጸጉ የቴክኖሎጂ አማራጮችን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በቴክኖሎጂ በመታገዝ የሚደረጉ የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴዎች የሳይበር ጥቃት እንዳይደርስባቸው የ24 ሰዓት ጥበቃ እየተደረገላቸው ነው ብለዋል።

ኤጀንሲው የሳይበር ጥቃት የመከላከሉን ስራ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ከባለድርሻ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዘርፉ ልምድ ካላቸው ሀገሮች ተሞክሮ በመውሰድ በሰው ሃብት ልማትና መሰረተ ልማት ግንባታ እንዲሁም የዲጂታል ግንዛቤ ማስፋት ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በአገር በቀል ምጣኔ ሃብት አጀንዳ ላይ የተመሰረተ የ 'ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025' ስትራቴጂ ቀርጻ ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረች አንድ ዓመት አስቆጥራለች።

በስትራቴጂው መሰረትም በሀገር አቀፍ ደረጃ  የንግድ፣ አገልግሎትና ሌሎች ተግባራት ከወረቀት ነጻ በሆነ አግባብ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ማከናወን የሚያስችል ዘመናዊ አሰራር የሚዘረጋ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም