ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ቋሚ ዘጋቢ ጋዜጠኞች እና ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሰራተኞች አረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ

138

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 19/2013 ( ኢዜአ) የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የአገር ውስጥና የውጪ መገናኛ ብዙሃን ቋሚ ዘጋቢ ጋዜጠኞች እና የጽህፈት ቤቱ ፕሬስ ሴክሬታሬያት ሰራተኞች አረንጓዴ አሻራቸውን ዛሬ በሚሊንየም ፓርክ አካባቢ አኑረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ "የ2013 የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር" ባለፈው ግንቦት በይፋ ከተጀመረ በኋላ በርካታ ተቋማትና ግለሰቦች የዛፍ ችግኞችን በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን እያሳረፉ ነው።

በዛሬው ዕለትም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ቋሚ ዘጋቢ የሆኑ የአገር ውስጥና የውጪ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን ጭምር የጽህፈት ቤቱ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሰራተኞች አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

ዛሬ ማለዳ በየካ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ሚሊንየም ፓርክ አካባቢ ባለ ስፍራ ነው ችግኝ ተከላ ያካሄዱት።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት የውጭ ቋንቋዎችና ዲጂታል ሚዲያ ዘርፍ ሃላፊ ቢለኔ ስዩም እንደገለጹት፤ በአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ጋዜጠኞች ከመዘገብ ባሻገር የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማድረግ የተዘጋጀ መርሀ ግብር ነው።

ጋዜጠኞች የራሳቸውን አሻራ በሚያሳርፉበት ወቅት ህብረተሰቡን ማነቃቃት የሚችሉ በመሆኑ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብሩ እንደተዘጋጀ ተናግረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ልዩ ልዩ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትን በመወከል ቋሚ ዘጋቢ ከሆኑ ጋዜጠኞች መካከል  አቶ አላዛር ታደለ፣ አቶ አስማማው አየነው እና አቶ አስታርቃቸው ወልዴ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ሲሳተፉ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ሲዘግቡ ቆይተዋል።

ዛሬ ደግሞ እነርሱ እንደ ዜጋ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት በችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ላይ መሳተፋቸውን ገልፀዋል።

ችግኝ መትከል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ጠቁመው፤ ሁሉም ችግኝ በመትከል የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻው አካል እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

“ኢትዮጵያን እናልብሳት” የ2013 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ባለፈው ግንቦት ወር በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በይፋ መጀመሩ የሚታወስ ነው።

በዚህ ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ ስድስት ቢሊዮን ችግኝ የሚተከል ሲሆን፤ ለጎረቤት አገሮች ደግሞ አንድ ቢሊዮን ችግኝ መዘጋጀቱ ተዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም