ከኦነግ ጋር የተደረሰው ስምምነት የዴሞክራሲ ስርዓቱን ወደ ተሻለ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግረው የጊምቢና ደምቢ ዶሎ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

71
ጊምቢ ነሀሴ 2/2010 የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በሰላማዊ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ገብቶ ለመንቀሳቀስ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር መስማማቱ የአገሪቱን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋጋር እንደሚያግዝ የጊምቢና ደምቢ ዶሎ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ። ኢዜአ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንዳሉት የኦነግ አመራሮች ወደ አገራቸው ገብተው በሰላማዊ ትግል ለመንቀሳቀስ መወሰናቸው አገሪቱ ወደ ላቀ የዴሞክራሲ ስርዓት እየተሸጋገረች መሆኗ አንድ ማሳያ ነው። የኢትዮጵያ መንግስትና ኦነግ ለበርካታ ዓመታት በመካከላቸው ነበረን አለመግባባት  በሰላማዊ መንገድ መፍታታቸው የፖለቲካ ምህዳሩ እየሰፋ መምጣቱንም እንደሚያሳይ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል። ከጊምቢ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ መኮንን ባይሳ ለዘመናት መሳሪያ በመታጠቅ በውጭ አገራትና በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ህጋዊ ያልሆነ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ኦነግ ከእዚህ ከድርጊቱ ለመታቀብ መስማማቱን እንደሚደግፉ ተናግረዋል። "ኦነግ ለብዙ ዓመታት በትጥቅ ትግል ውስጥ ቆይቶ አገሪቱ በለውጥ እንቅስቃሴ ላይ ባለችበት በአሁኑ ወቀት ወደ ሰላማዊ ትግል ለማድረግ መወሰኑ ያስመሰግነዋል" ያሉት ሌላው የጊምቢ ከተማ ነዋሪ አቶ አብረሃም ዲቢሳ ናቸው። ግንባሩ ችግሮችን በሰለጠነ መንግድ በውይይት በመፍታት ሰላማዊ ትግልን በአገር ውስጥ ለመጀመር ማቀዱን እንደሚያደንቁም ተናግረዋል። እንደ አቶ አብረሃም ገለጻ በምዕራብ ወለጋና አካባቢው ባለፉት ጥቂት ወራት የኦነግ ታጣቂዎች ይንቀሳቀሳሉ ተብሎ በመወራቱ ህዝቡ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ገብቶ ነበር። በአሁኑ ወቅት ኦነግ ሰላማዊ ትግልን መምረጡ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ትልቅ መረጋጋት ይፈጥራል የሚል እምነት እንዳለውም ተናግሯል። በደምቢ ዶሎ ከተማ የሚኖሩት አቶ ተፈሪ ድና በበኩላቸው "በኢትዮጵያ መንግስትና በኦነግ መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ኢትዮጵያዊያን ችግራችንን በራሳችን መፍታት እንደምንችል ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ሌላ ማሳያ ይሆናል" ብለዋል። የኦነግ አመራሮች ወደ አገር ውስጥ ገብተው ከመንግስት ጋር የሚያደርጉት ተጨማሪ ውይይት እንዲሳካና ግንባሩም እንደማንኛውም ተፎካካሪ ፓርቲ በአገሪቱ ፖለቲካ ጉዳዮች ላይ መሳተፍ እንዲችል አገራዊ ለውጡ ሊጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም