በኦሮሚያ ከሶስት ዞኖች ለሰራዊቱ 77 ሰንጋዎችና 35 በጎች ድጋፍ ተደረገ

727

ጎባ፣ነቀምት፣ነገሌ ሐምሌ 17/2013(ኢዜአ) በአሮሚያ ባሌ፣ ምስራቅ ወለጋና ጉጂ ዞኖች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት 77 ሰንጋዎችንና 35 በጎች ድጋፍ መሰባሰቡ ተገለጸ።

በባሌ ዞን የሮቤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ገዛሄኝ ደዳኔ እንዳመለከቱት የከተማዋን ነዋሪ በማስተባበር ለሰራዊቱ ድጋፍ የሚውል 32 ሰንጋዎች ማሰባሰብ ተችሏል።

“ድጋፉ ሕዝቡ የሀገር ሉዓላዊነት ዓርማ የሆነውን የመከላከያ ሰራዊት ጎን መሆኑን ማሳያ ነው” ብለዋል።

በድጋፉ የተገኙት ሰንጋዎች አንድ ሚሊየን ብር እንደሚገመት የገለጹት ከንቲባው፤ ህግ የማስከበር ዘመቻው በድል እስከሚጠናቀቅ ድጋፉ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ከሮቤ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ኢሳ መሐመድ በሰጡት አስተያየት፤የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለማስከበር መስዋዕትነት እየከፈለ የሚገኘውን የመከላከያ ሰራዊት በሚፈለገው ሁሉ ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

መንግስት የውጭና የውስጥ ጫናዎችን በመቋቋም የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለማስከበር እያደረገ የሚገኘውን ዘመቻ መደገፋቸውን እንደሚያጠናክሩ የተናገሩት ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ መንደሪና ሁሴን ናቸው።

በተመሳሳይ ከምሥራቅ ወለጋ ዞን ህብረተሰብ 25  ሰንጋዎችንና 35 በጎችን ድጋፍ መገኘቱን  የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ደረጀ አበራ አስታውቀዋል።

አቶ ደረጀ  እንዳሉት፤ ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት እየተደረገ ያለው ድጋፍ የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ አይደለም።

የአካባቢው ባለሀብቶችና ድርጅቶች በድጋፍ የተገኙትን ሰንጋዎች የሀገር መከላከያ ሠራዊት ባለበት ቦታ ለማድረስ ዝግጁ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

ከነቀምቴ ከተማ አስተዳደር  ደግሞ  14 ሰንጋዎችን ድጋፍ  መገኘቱን  የብልጽግና ፓርቲ የከተማ አስተዳደሩ ጽህፈት ቤት  የፖለቲካ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደሣለኝ ቦጎንጃ ገልጸዋል።

የአስተዳደሩ ነዋሪ ሀዝብ ከሀገር መከላከያ ሠራት ጎን መቆሙን ለማሳየት  ያደረገ ይሄው ድጋፍ የሕወሐት ጁንታ እስኪደመሰስ  ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

በጉጂ ዞን የአዶላ ከተማ ነዋሪዎችና ባለሀብቶች ለመከላከያ ሰራዊቱ ስድስት ሰንጋዎችን ድጋፍ ማድረጋቸውን የከተማው አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኡቱራ አመዩ ገልጸዋል።

ድጋፉ የከተማዋ አስተዳደር ባለሀብቶች  እስከ ግንባር በመሄድ ለሰራዊቱ ለማስረከብ መሰናዳታቸውን ተናግረዋል፡፡

ህዝብን ከህዝብ በመከፋፈል ሀገር ለማፍረስ የተነሳውን የሽብር ቡድን ለመከላከል ህዝቡ የጀመረውን ድጋፍና ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥልም ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከከተማዋ  ባለሀብቶች መካከል አቶ ገነነ ሽብሩ  በሰጡት አስተያየት፤ የህወሀት የሽብር ቡድን ህጻናትን ለጦርነት በማሰለፍ ሀገር ለማፍረስ የጀመረው ሴራ አይሳካም ብለዋል፡፡

በውጭ ጫናና ተጽዕኖ የሚከፋፈል ህዝብና የሚፈርስ ሀገር እንደሌለ  የውስጥም የውጭም ጠላት ሊገነዘብ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የከተማዋ ነዋሪ  አቶ አየለ ኡዶ በበኩላቸው፤ የሽብር ቡድኑ ህጻናትና አዛውንቶችን ከፊት በማሰለፍ ለሞት በመዳረጉ ማዘናቸውን ገልጸዋል፡፡

ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን በመሆን ሀገርን ከጥፋት ለመታደግ   ድጋፋቸውን አጠናክረው ለመቀጠልም ቃል ገብተዋል፡፡