ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ በቶኪዮ ኦሊምፒክ የነገውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመራል

120

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17 ቀን 2013 (ኢዜአ) ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ በ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች በእግር ኳስ ውድድር ነገ ስፔንና አውስትራሊያ የሚያደርጉትን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመራል።

32ኛው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታ በይፋዊ መክፈቻ ስነ ስርዓት ትናንት ተጀምሯል።

ይሁንና ከመክፈቻው ስነ ስርዓት በፊት የሴቶች እግር ኳስ ውድድር ሐምሌ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን፤ የወንዶች እግር ኳስ ውድድር ከትናንት በስቲያ ተጀምሯል።

ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) በሚያዚያ 2013 ዓ.ም በቶኪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች በእግር ኳስ ውድድር እንዲያጫውቱ ከመረጣቸው ዋና ዳኞች መካከል ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ እንዱ ሆኖ መመረጡ ይታወሳል።

በዚሁ መሰረት ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ነገ በወንዶች የእግር ኳስ ውድድር በምድብ ሶስት አውስትራሊያና ስፔን የሚያደርጉትን ጨዋታ በዋና ዳኝነት እንደሚመራ ከፊፋ ድረገጽ ላይ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ነገ ከምሽቱ 12 ሠዓት ከ30  ላይ 41 ሺህ 484 ተመልካች በሚያስተናግደው ሳፖሮ ዶሜ ስታዲየም በሚደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ የመሐል ዳኛ ሆኖ ያጫውታል።

ይህም ለኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች በዋና ዳኝነት ሲያጫውት ለመጀመሪያ ጊዜ ይሆናል።

የ40 ዓመቱ ኢንተርናሽናል ዳኛ በፊፋ የኢንተርናሽናል ዳኝነት ባጅ ያገኘው እ.አ.አ በ2009 ሲሆን ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ውድድሮች በመዳኘት የረጅም ጊዜ ልምድ አካብቷል።

እ.አ.አ በ2018 በሩሲያ አስተናጋጅነት በተካሄደው 21ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ውድድሩን እንዲያጫውት ቢመረጥም በውድድሩ በዋና ዳኝነት የመራው ጨዋታ አልነበረም።

የቶኪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች የሴቶች እግር ኳስ ውድድር ሐምሌ 29 ቀን 2013 ዓ.ም የሚጠናቀቅ ሲሆን  የወንዶች እግር ኳስ ውድድር ደግሞ ነሐሴ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ፍጻሜውን ያገኛል።

የሴቶች እግር ኳስ ውድድር በሶስት ምድቦች በ12 ብሔራዊ ቡድኖች መካከል የሚካሄድ ሲሆን፤ የወንዶቹም በአራት ምድብ በ16 ብሔራዊ ቡድኖች መካከል የሚከናወን ነው።

32ኛው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች እስከ ነሐሴ 2 ቀን 2013 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም