ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት ኃላፊን አነጋገሩ

923

አዲስ አበባ ነሃሴ 2/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት ኃላፊ ፔኒ ሞርዳንት ጋር ተወያዩ።

ድርጅቱ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ኃላፊዋ አስታውቀዋል።

ፔኒ ሞርዳንት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ያካሄዱት ውይይት በሁለትዮሽ ምጣኔ ኃብታዊ የትብብር ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደነበርም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

በዚሁ ጊዜ ፔኒ ሞርዳንት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ አድንቀዋል። የሚመሩት የልማት ድርጅትም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ የታክስ አሰባሰብ ስርዓትን ለማጠናከር የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ እንዲቻልም በእንግሊዝ መንግስት ድጋፍ የተቀረፀ ፕሮግራም ፔኒ ሞርዳንት በተገኙበት ዛሬ በአዲስ አበባ ይፋ ይደረጋል።

ፕሮግራሙ የኢትዮጵያ መንግስት የታክስ አሰባሰብ አቅም እንዲጎለብት እና ገቢው እንዲጠናከር በማድረግ የሀገሪቱን የልማት ውጥኖች በራስ ገቢ ለማከናወን የሚያስችል ሁኔታን ለመፍጠርና በእርዳታ ላይ ሊኖር የሚችልን ጥገኝነት ለማስወገድ የሚያግዝ ነው ተብሏል።

በሌላ በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል የኤንዶኔዥያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዱራህማን ሞሐመድ ፋቺርን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

መሪዎቹ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መጠናከር በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥተው መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ  ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

በኢትዮጵያና በኢንዶኔዥያ መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት እና የመሰረተ ልማት ግንባታ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም መክረዋል፡፡

የኢንዶኔዥያ የመሰረተ ልማት እና የገንዘብና ኢኮኖሚ ባለሙያዎች የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ልማት አጀንዳዎች ሊደግፉ በሚችሉበት መንገድ ላይም ተወያይተዋል።

ኢትዮጵያ እና ኢንዶኔዥያ በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት የአገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል በዚሁ ጊዜ ገልፀዋል።

የኢንዶኔዥያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዱራህማን ሞሐመድ ፋቺር በበኩላቸው ሀገራቸው በመሰረተ ልማት ግንባታ ኢትዮጵያ ውስጥ ተሳትፎ ማድረግ እንደምትፈልግ ተናግረዋል።