ኢትዮጵያ ለዲጂታል ምጣኔ ሃብት መሰረት የሚሆን አዲስ ሥርዓት ፈጥራለች...ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር

147

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያ ባለፈው አንድ ዓመት ለዲጂታል ምጣኔ ሃብት መሰረት የሚሆን አዲስ ሥርዓት መፍጠሯን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 አካል የሆነውን የ"ዲጂታል ኢትዮጵያ፤ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ"  ስትራቴጂ የአንድ ዓመት ክንውንና ቀጣይ ሥራዎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ገምግሟል።

ሚኒስቴሩ በአንድ ዓመት ውስጥ ያከናወናቸውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ትግበራ አፈጻጸም የሚያሳይ ሪፖርትም ቀርቧል።

ሪፖርቱን ያቀረቡት በሚኒስቴሩ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር አብዮት ባዩ የተከናወኑ ተግባራትን ዘርዝረዋል።

የኢትዮጵያን ምጣኔ ሃብት ለማፋጠን የተቀረጸው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ መሠረቱን የአገር በቀል ምጣኔ ሃብት እድገትን አጀንዳ ማድረጉን አውስተዋል።

የቴሌኮም ሪፎርምን ማፋጠን፣ ሥራ ፈጣሪዎችን መደገፍ፣ ኢ-ኮሜርስና ዲጂታል ክፍያን ማስፋት፣ ግንዛቤ ማሳደግና ሌሎችም ተግባራትን ማከናወን የተቀመጡ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ሲሆኑ በአንድ ዓመት የተከናወኑ ተግባራትን አብራርተዋል።

ከመሠረተ ልማት አንጻር የቴሌኮም ሪፎርም አይነተኛ ሚና መጫወቱንና በኢትዮ-ቴሌኮም በኩል የተደረገው ማሻሻያ ለዲጂታል ምጣኔ ሃብት መፋጠን ያለውን ጠቀሜታም አስረድተዋል።

ስትራቴጂው ሲቀረጽ ያልነበሩ መሠረተ ልማት፣ የህግ ማእቀፎች፣ አዋጆችና ሌሎች ለዲጂታል ምጣኔ ሃብት እድገት መሰረት የሚሆን አዲስ ዓለም መፈጠሩንም አክለዋል።  

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ በበኩላቸው፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ለምጣኔ ሃብት፣ ለሥራ እድልና ለሃብት ፈጠራ ያለውን ሚና እውን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአንድ ዓመት ውስጥ ለሚመለከታቸው አካላት ግንዛቤ መፍጠርና የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀትን ጨምሮ ተቋማት የእቅዳቸው አካል እንዲያደርጉት ሥራዎች መከናወናቸውን አውስተዋል።

በቀጣይ የዲጂታል ጉዞን ለማሳካት የተጀመሩ ሥራዎችን በማጠናከር ያልተጀመሩትን ደግሞ በመጀመር  በትኩረት መሥራት እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።

በመድረኩ የተገኙ ተቋማት በአንድ ዓመት ውስጥ ለዲጂታል ምጣኔ ሃብት ግንባታ እያከናወኗቸው ያሉ ተግባራትን አቅርበዋል።

በመሰረተ ልማት፣ በአስቻይ ሁኔታዎች፣ በተግባራዊነት፣ በፋይናንስ፣ በሰው ሃብት ልማትና የሥራ እድል ፈጠራ በአስቻይ የህግ ማዕቀፎችና ትብብር ላይ ያከናወኗቸውን ተግባራት በመድረኩ ቀርቧል።

ከእነዚህ መካከል የሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽነር ንጉሱ ጥላሁን እና የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ በተቋሞቻቸው የተከናወኑ ተግባራትን ገልጸዋል።

የዲጂታል መሰረተ ልማትና ትስስርን ማጠናከር፣ ግንዛቤን ይበልጥ ማስፋትና ሌሎችም በቀጣይ በትኩረት የሚከወኑ ተግባራት ሲሆኑ የፋይናንስ እጥረትና ሌሎች ሊያጋጥሙ የሚችሉ ስጋቶችም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም