በደቡብ ክልል ለሠራዊቱ ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ በዓይነትና ጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ተሰበሰበ

ሀዋሳ፤ ሐምሌ 17/2013 (ኢዜአ )የደቡብ ክልል ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ በዓይነትና ጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰቡ ተገለጸ።

የደቡብ ክልል የሀብት አሰባሰብ ፋይናንስና ሎጀስቲክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፋጤ ሶርሞሎ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ የክልሉ ህዝብ ለሀገር መከላከያ ኃይል በተለያየ መንገድ የደጀንነት ድጋፉን አጠናክሮ ቀጥሏል።

በተለይ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ከአንዳንድ ምዕራብያዊያን ሀገራት ጋር በመመሳጠርና በሀገር ውስጥም ሴሎችን በመፍጠር ኢትዮጵያን ለውጭ ሀይሎች አሳልፎ ለመስጠት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ በክልሉ ህዝቦች ዘንድ ቁጣ መቀስቀሱን ገልጸዋል።

በዚህ ድርጊት ቁጭት ውስጥ የገባው መላው የክልሉ አርሶና አርብቶ አደሩ፣ ባለሀብቱ፣ የከተማው ነዋሪ፣ የመንግስት ሰራተኛው፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ ወጣቶችና ሴቶች ግንባር ላይ ለሚገኘው ሠራዊት ደጀንነታቸውን ለመግለጽ በዓይነትና ጥሬ ገንዘብ ድጋፍ እያደረጉ ናቸው ብለዋል።

በክልሉ ሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በተካሄደው እንቅስቃሴ 14 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብና 4 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር የሚገመት ደግሞ በዓይነት መገኘቱን አስታውቀዋል።

ከህዝቡ የተገኘውን ይህንኑ ድጋፍ ወደ ግንባር ለማድረስ ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰው ድጋፉ ቀጣይነት እንዳለውም ገልጸዋል።

በምግብ ስንቅ ዝግጅት በመሳተፍ ላይ ከሚገኙት አንዷ የሆኑት ወይዘሮ ነኢማ ሙኒር ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ሀገርን ለማፍረስ የሚንቀሳቀሰው ጁንታ ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ ለመደገፍ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሌላዋ የስንቅ ዝግጅቱ ተሳታፊ ወይዘሮ ፀዳለች ሚካኤል በበኩላቸው፤ በግንባር ላይ እየተዋደቀ ለሚገኘው መከላከያ ሠራዊታችን ጎን መሆናችንን ለመግለጽ ለትግሉ አጋዥና ወሳኝ የሆነውን ስንቅ ለማቀበል እየተጋን ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል የደቡብ ክልል የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ያዘጋጁትንና ያሰባሰቡትን ቁሳቁስና ሀብት ለክልሉ ሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ አስረክበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም